Amharic Health Information

ላይስኖፕሪል (Lisinopril)

የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ ላይስኖፕሪል (Lisinopril)

ምድብ፦ ኤሲኢ ኢንሂቢተር (ACE inhibitor)

ብራንድ ስም ዘስትሪል (Zestril) 

ላይስኖፕሪል (Lisinopril) ለምን ይታዘዛል?

ይህ መድሃኒት ከፍተኛ ደም ግፊት ለማስተካከል የሚታዘዝ መድሃኒት ነው። እንዲሁም ለሌሎች ህመሞች ሊታዘዝ ይችላል። ለምሳሌ፦

  • ለልብ ድካም (Heart failure)
  • ለልብ በሽታ (Acute Myocardial Infraction)

ላይስኖፕሪል እንዴት ነው የሚሰራው?

ላይስኖፕሪል (Lisinopril) የደምስር እንዲሰፋ በማድረግ ከፍተኛ የደም ግፊትን ያስተካክላል። ይህን የሚያደርገው አንጂዮቴንሲን ቀያሪ ኢንዛይም (Angiotensin-converting enzyme (ACE)) እንዳይሰራ በማድረግ ነው። አንጂዎቴንሲን ቀያሪ ኢንዛይም የአንጂዎቴንሲን-ሬኒን ስርአት( Angiotensin-renin system) አካል ሲሆን የሚጠቅመው አንጂዎቴንሲን አንድ(Angiotensin I) የሚባለውን ንጥረ ነገር ወደ አንጂዎቴንሲን ሁለት (Angiotensin II) ለመቀየር ነው።  አንጂዎቴንሲን ሁለት  የደም ቧምቧዎችን በማጥበብ የደም ግፊት እንዲጨምር ያደርጋል። በተጨማሪ የደም ግፊት እንዲጨምር የሚያደርጉ ሌሎች ኬሚካሎች እንዲመነጩ ያደርጋል። ላይስኖፕሪል አንጂዮቴንሲን ቀያሪ ኢንዛይም እንዳይሰራ በማድረግ አንጂዎቴንሲን ሁለት  (Angiotensin II) እንዳይመረት ያደርጋል። ስለዚህም በአንጂዎቴንሲን ሁለት ምክንያት የሚከተለውን ከፍተኛ የደም ግፊትን ያስተካክላል።

ላይስኖፕሪል በምን መልኩ ታሽጎ ይመረታል?

 በአፍ የሚዋጥ ክኒን

ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎ

  • በእርግዝና፦ ላይስኖፕሪል በጽንስ ጤንነት ላይ ጉዳት ሊያመጣ እና ሞት ሊያስከትል ይችላል። ለመጸነስ ሲያስቡ ወይም እርጉዝ እንደሆኑ ካወቁ ለሃኪምዎ ያሳውቁ።
  • የከንፈር፣ የምላስ፣ የእግር፣ የጉሮሮ ማበጥ ወይም አንጂዮኢዲማ (Angioedema) ይህ ከላይስኖፕሪል የተያያዘ የሰውነት ክፍል ማበጥ በአንዳንድ ላይስኖፕሪል በሚወስዱ ህመምተኞች ላይ ሊከሰት ይችላል። ይህ እብጠት በፍጥነት ወይም ቀስ ብሎ ሊያድግ ይችላል። ነገር ግን በአንዳንድ ሰዎች ላይ ከባድ የጤና ችግር ሊያስከትል ስለሚችል ይህ እብጠት ከተከሰተ ቶሎ መድሃኒቱን መተው እና ወደሀኪም መሄድ ይመከራል። በዚህ ምክንያት ላይስኖፕሪን (ወይም በዚህ ምድብ ውስጥ ያሉ መድሃኒቶች) ካቆሙ ድጋሚ እንዳይታዘዝልዎት ለሀኪምዎ ያሳውቁ።
  • ሳል፦ ይህን መድሃኒት ሲወስዱ ጉሮሮ ላይ ብን ብን የሚል ሳል ሊከሰት ይችላል። ይህ ከሆነ ለሀኪምዎ ያማክሩ።
  • ላይስኖፕሪልን በሚወስዱበት ግዜ አልኮል መጠጣት አይመከርም።

ሌሎች ከዚህ መድሃኒት ጋር የሚጋጩ መድሃኒቶች

  1. ሊትየም (Lithium)፦ ላይስኖፕሪል በሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች ላይ የሊትየም መጠን በደም ውስጥ ሊጨምር ይችላል። ሊትየም የሚወስዱ ከሆነ ሃኪምዎ በየግዜው በደምዎ ያለውን የሊትየም መጠን በደም ምርመራ ይከታተላል። ስለዚህ የሀኪም ቤት ቀጠሮዎን አያሳልፉ። በተጨማሪ ሊትየም በሚወስዱበት ግዜ ተቅማጥ፣ ማስመለስ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት እንዲሁም ይህን ተከትሎ የእይታ ብዥ ማለት፣ ጆሮ ላይ ጭው የሚል ድምጽ መሰማት እና የሽንት መብዛት ከተሰማዎት የሊትየም በሰውነትዎ ውስጥ መብዛቱን ሊያመላክት ይችላልና ወደሃኪም መሄድ ያስፈልጋል።
  2. ፓታስየም (Potassium)፦ ይህን መድሃኒት የሚወስዱ አንዳንድ ህመምተኞች በደማቸው ውስጥ ፓታስየም የተባለ ንጥረነገር ሊጨምር ይችላል። ይህ በልብ እና በሌላ ሰውነት ላይ ችግር ሊያመጣ ይችላል። የፓታስየም መጨመር አልፎ አልፎ የሚከሰት ቢሆንም የኩላሊት ህመም፣ ሌሎች መድሃኒቶች፣ እና የስኳር በሽታ እድሉን ሊያሰፋው ይችላል። ይህን ለመከላከል ሃኪም ሳያዝልዎ የፓታስየም ክኒኖችን አይውሰዱ። በተጨማሪ በጨው ምትክ ምግብ ውስጥ የሚጨመሩ የፓታስየም ጨው(አርቴፊሻል ጨው) አይጠቀሙ። ሃኪምዎ በየግዜው የደምዎን ፓታስየም መጠን በደም ምርመራ ስለሚያይልዎት የሃኪም ቤት ቀጠሮዎን ይከታተሉ።

የላይስኖፕሪል ትክክለኛ አወሳሰድ

  • ሀኪምዎን ትእዛዝ በጥንቃቄ ይከተሉ።
  • ብዙ ግዜ ላይስኖፕሪል በቀን አንድ ግዜ ይወሰዳል። ቀንም ሆነ ማታ መውሰድ ይቻላል። በየእለቱ በተመሳሳይ ሰአት መዋጥ መድሃኒትዎን ሳይረሱ እንዲወስዱ ይረዳዎታል።
  • ከምግብ በፊት ወይም በሃላ መውሰድ ይቻላል።

መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?

ወድያው እንዳስታወሱ ይውሰዱ። ብዙ ሰአት ካለፈ ይተውት እና በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ግዜዎ የተለመደውን መጠን ይዋጡ። የረሱትን ጨምረው ለመዋጥ አይሞክሩ።። ለሀኪምዎ ሳያማክሩ ድንገት መድሃኒትዎን መውሰድ አያቁሙ።

በዚህ መድሃኒት ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች

ይህን መድሃኒት መውሰድ ሲጀምሩ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ድካም ድካም ማለት፣ ራስ ምታት፣ ራስ ማዞር፣ ሳል እና ተቅማጥ ሊከሰት ይችላል። ሰውነት ሲላመድ ቀስ በቀስ እነዚህ ስሜቶች እየቀነሱ ይመጣሉ። ነገር ግን ከሚችሉት በላይ ከሆነ ለሀኪምዎ ያማክሩ። መድሀኒቱን መውሰድ እንደጀመሩ ድካም እና የራስ ማዞር ከተሰማዎት መድሃኒቱ ከፍተኛ ደም ግፊትን ሲቀንስ የሚያሳየው ባህሪ ነው።

መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ

መድሃኒትዎን ሙቀት እና ቅዝቃዜ የማይበዛበት  ደረቅ ቦታ ያስቀምጡ። መድሃኒትን መታጠቢያ ቤት ማስቀመጥ አግባብ  አይደለም። ህጻናት እና የቤት እንስሳት የማይደርሱበት ቦታ ያስቀምጡ።

ኩፓኖች

GoodRX ድረገጽ በመሄድ ኩፓን ማተም ይችላሉ

ማውጫ