የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ ድሮስፓይርኖን/ኤትናይል ኤስትርዳዮል (Drospirenone/ethinyl estradiol)
ምድብ፦ ፕሮጀስቲን/ኤስትሮጅን ሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያዎች
ብራንድ ስሞች፦ ያዝምን (Yasmin) ዛራሀ (Zarah) ሳይዳ (Syeda) ኦሴላ (Ocella)
ድሮስፓይርኖን/ኤትናይል ኤስትርዳዮል ለምን ይወሰዳል?
ድሮስፓይርኖን/ኤትናይል ኤስትርዳዮል እርግዝናን ለመከላከል ይረዳል።
እንዴት ነው የሚሰራው?
በአፍ የሚወሰዱ የወሊድ መቆጣጠሪያ ክንኖች እንቁላል ወደ ማህፀን እንዳይወጣ በማድረግ (by preventing ovulation) እርግዝናን ይከላከላሉ። በተጨማሪ ጽንስ እንዳይፈጠር የማህጸን ግድግዳ እና የማህጸን ፈሳሽ ላይ ተጽእኖ ያደርጋሉ። ይህ ክኒን ሁለት መድሀኒቶችን በውስጡ ይይዛል። የመጀመሪያው ድሮስፓይርኖን (Dospirenone) ሲሆን ሁለተኛው ኢትናይል ኤስትርዳዮል (Ethinyl estradiol) ነው።
ኢትናይል ኤስትርዳዮል (Ethinyl estradiol) በተፈጥሮ የሚገኘውን ኤስትሮጅን (estrogen) ሆርሞን የሚመስል ንጥረ ነገር ሲሆን ድሮስፓይርኖን (Dospirenone) ፕሮጀስቲን (progestin) የሚባለውን ሌላ ሆርሞን እንዲመስል ተደርጎ የተሰራ ንጥረ ነገር ነው። እነዚህ ሆርሞኖች በጉርምስና ወቅት በሴቶች እና በወንዶች ላይ የሚታየውን ለውጥ ጨምሮ በሴቶች የወር አበባ ኡደት፣ በእርግዝና፣ በአጥንት ጤንነት፣ በሜታቦሊዝም ላይ ከፍተኛ አስተዋእፆ አላቸው።
በምን መልኩ ተመርቶ ይታሸጋል?
በአፍ የሚዋጥ ክኒን
ለዚህ ጽሁፍ እንደምሳሌ የምንወስደው የያዝምንን ክኒኖች ቀለም ነው። ለአንድ ወር የሚሆን የያዝምን ብሊስተር ካርድ ሀያ አንድ ቢጫ ክኒኖች እና ሰባት ነጭ ክኒኖች ይኖሩታል። ነገር ግን እንደአገሩ እና እንዳአምራቹ የተለያየ ቀለም ያላቸው ክኒኖች ይኖራሉ። ለምሳሌ የዛራሀ ክኒኖች ሀያ አንድ ሰማያዊ እና ሰባት ቢጫ ክኒኖች አሉት።
ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ምንድነው?
- ይህ መድሀኒት እርግዝና ለመከላከል የሚረዳው በየእለቱ በተመሳሳይ ሰአት ሲወሰድ ብቻ ነው። እንዳይረሱ ጥረት ያድርጉ። ከረሱ “መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?” የሚለውን ክፍል ያንብቡ ወይም የጤና ባለሙያ ያማክሩ።
- ይህን መድሀኒት መውሰድ እንደጀመሩ ለመጀምሪያው ሳምንት እርግዝናን ላይከላከል ይችላል። በዚህ የመጀምሪያ ሳምንት ተጨማሪ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገድ (ለምሳሌ ኮንዶም) ይጠቀሙ።
- መድሀኒትዎን መውሰድ ከመጀምርዎ በፊት የመድሀኒቱ ካርድ ሀያ ስምንት ክኒን እንዳለው ያረጋግጡ። ብዙ ግዜ ብሊስተር ካርዱ ላይ ከየት መጀመር እንዳለብዎት የሚያመላክት ቀስት ይኖራል። በተጨማሪም ለማስታወስ እንዲረዳ የመድሀኒቱ ካርድ ላይ የክኒኖቹ አቀማመጥ በቀን እና በሳምንት ተስተካክሎ ይገኛል (ከታች የሚገኘውን ምስል ይመልከቱ።)
- ዘወትር የሚያገኙት ቦታ ሌላ ተጨማሪ የወሊድ መቆጣጠሪያ (ለምሳሌ ኮንዶም) ያስቀምጡ። ክኒኑን መውሰድ የሚዘነጉበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ይጠቅማል።
- እርግዝና ከተከሰተ መድሀኒቱን መውሰድ ያቁሙ። መድሀኒቱ በጽንስ ላይ ጉዳት አያደርስም (አያስወርድም)። ነገር ግን ከእርግዝና በሁዋላ ይህን መድሀኒት መውሰድ አስፈላጊ አይደለም።
- የሚያጠቡ እናቶች ይህን መድሀኒት ሲወስዱ የጡት ወተት ይቀንሳል። በተጨማሪ መድሀኒቱ በጡት ወተት ውስጥ ሊኖር ይችላል። ስለዚህ አማራጭ ለማግኘት የጤና ባለሙያዎትን ይጠይቁ።
ድሮስፓይርኖን/ኤትናይል ኤስትርዳዮል የማይታዘዝላቸው ሴቶች
ከሚከተሉት ህመሞች ወይም ሁኔታዎች የሚያጋጥማቸው ሴቶች ይህ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሀኒት ላይታዘዝላቸው ይችላል። ይህም የሚደረገው ይህ መድሀኒት እነዚህን በሽታዎች እንደገና ሊቀሰቅሱ ወይም ሊያባብሱ ስለሚችሉ ነው። ስለዚህም ስለወሊድ መቆጣጠሪያ ከጤና ባለሙያ ጋር ሲነጋገሩ ያለብዎትን የጤና እክል በግልጽ ያማክሩ
- የኩላሊት በሽታ (Renal impairment)
- አድሬናል ህመም (Adrenal insufficiency)
- የደም መርጋት በሽታ (Thrombotic diseases) ወይም ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ሁኔታዎች ካሉ
- ሲጃራ የምታጨስ (ትምባሆ የምትጠቀም) እና ከሰላሳ አምስት አመት እድሜ በላይ ከሆነች
- የልብ ደምስር በሽታ (Coronary artery disease) ለምሳሌ የልብ በሽታ (heart attack)
- የአንጎል ደምስር በሽታ (Cerebrovascular disease) ለምሳሌ ስትሮክ
- በዘር የሚመጣም ሆነ ሌላ አይነት ቶሎ ደም የመጓጎል የሚያስከትሉ በሽታዎች (Hypercoagulopathies)
- በስኳር በሽታ ምክንያት የመጣ የደምስር በሽታ (Diabetes with vascular disease)
- በህክምና ሊስተካከል ያልቻለ ከፍተኛ ደም ግፊት
- ማይግሬን (Migraine) ወይም የራስምታት ያለባት ሆኖ ከሰላሳ አምስት አመት እድሜ በላይ ከሆነች
- ምክንያቱ ያልታወቀ ከወር አበባ ጋር ያልተገናኘ የማህጸን ደም መፍሰስ
- የጡት ካንሰር ወይም በኤስትሮጅን ወይም በፕሮጀስቲን ምክንያት ሊባባስ የሚችል ካንሰር
- የጉበት እጢ (Liver tumor)
ይህ መድሀኒት በትክክል እንዳይሰራ የሚያደርጉ መድሀኒቶች
አንዳንድ መድሀኒቶች የዚህን መድሀኒት የእርግዝና መከላከል ችሎታ ሊቀንሱ ይችላሉ። ለኢንፌክሽን የሚታዘዙ ብዙ አንቲባዮቲክ (antibiotic) መድሀኒቶች ይህ ባህሪ ስላላቸው መድሀኒትዎን ከፋርማሲ ሲገዙ በአፍ የሚዋጡ ወሊድ መቆጣጠሪያ መድሀኒት ላይ ተጽእኖ እንደሌለው ፋርማሲስትዎን ይጠይቁ። ሌሎች ይህን መድሀኒት ሀይል ሊቀንሱ የሚችሉ መድሀኒቶች የሚከተሉት ናቸው፦
- ባርቢቹሬት (Barbiturates)
- ቦሰንተን (Bosentan)
- ካርባማዘፒን (Carbamazepine)
- ፈልባሜት (Felbamate)
- ግሪዚዮፎልቨን (Griseofulvin)
- ኦክስካርባማዘፒን (Oxcarbazepine)
- ፌንቶይን (Phenytoin)
- ራይፋምፕን (Rifampin)
- ሴንት ጆንስ ዎርት (St. John’s wort)
- ቶፓይሪሜት (Topiramate)
እንዲህ ያሉ መድሀኒቶችን በሚወስዱበት ግዜ ተጨማሪ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶችን (ለምሳሌ ኮንዶም) ይጠቀሙ።
ትክክለኛ አወሳሰድ
ድሮስፓይርኖን/ኤትናይል ኤስትርዳዮል ለመጀመር ሁለት አማራጮች አሉ፦
- የመጀመሪያውን ቢጫ ክኒን የወር አበባ በሚታይበት የመጀመሪያው ቀን በመዋጥ መጀመር ይቻላል። ከዛ ቀጥሎ ላሉት ሃያ አንድ ቀኖች አንድ ቢጫ ክኒን በቀን አንድ ግዜ ይወሰዳል። ለሚቀጥሉት ሰባት ቀኖች (ማለትም የወር አበባ ከታየበት ከሃያ ሁለተኛው እስከ ሀያ ስምንተኛው ቀን) አንድ ነጭ ክኒን በቀን አንዴ ይዋጣል። በሀያዘጠነኛው ቀን አንድ ቢጫ ክኒን በመውሰድ የሚቀጥለውን ወር መጀመር ይቻላል። በዚህ መንገድ የጀመረች ሴት ለመጀምሪያው ሳምንት የወሊድ መቆጣጠሪያ አያስፈልጋትም።
- ሌላኛው መንገድ የመጀመሪያውን የወሊድ መቆጣጠሪያ ቢጫ ክኒን የወር አበባ በታየበት ሳምንት የመጀመሪያው እሁድ መዋጥ ይቻላል። ቀጥሎ ላሉት ሃያ አንድ ቀኖች አንድ ቢጫ ክኒን በቀን አንድ ግዜ ይወሰዳል። ለሚቀጥሉት ሰባት ቀኖች አንድ ነጭ ክኒን በቀን አንዴ ይዋጣል። በሀያ ዘጠነኛው ቀን አንድ ቢጫ ክኒን በመውሰድ የሚቀጥለውን ወር መጀመር ይቻላል። በዚህ መንገድ መጀምር ቅዳሜ እና እሁድ የወር አበባ እንዳታይ ይረዳል። ነገር ግን በመጀምሪያው ሳምንት ተጨማሪ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል።
መድሀኒቱን ምሽት ላይ ከምግብ በሁዋላ ወይም ከመኝታ በፊት መውሰድ ይመረጣል።
ይህን መድሀኒት ከምግብ ጋር ወይም ያለምግብ መውሰድ ይቻላል።
ድሮስፓይርኖን/ኤትናይል ኤስትርዳዮልን መውሰድ ከጀመሩ በሁዋላ የሚከሰቱ ነገሮች እና መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች
- ነጭ ክኒን ለሰባት ቀኖች ከተወሰደ በሁዋላ የወር አበባ ቢቆምም ባይቆምም በማግስቱ ቢጫ ክኒን መወሰድ አለበት።
- የመጨረሻው ቢጫ ክኒን ከተወሰደ በሁዋላ ከሶስተኛው ቀን አንስቶ ለተወሰነ ግዜ ደም ሊታይ ይችላል። ይህም መጠኑ እንደወር አበባ ያህል ሊሆን ወይም ትንሽ ደም መታየት ብቻ ሊሆን ይችላል። ይህም የተለመደ የመድሀኒቱ ባህሪይ ስለሆነ ክኒኑን መቀጠል ይቻላል። ነገር ግን ይህ ከተለመደው በላይ ከባድ ከሆነ ለሀኪም ማማከር ይኖርባታል።
- ይህ ደም በዚህ ግዜ ወይም ነጭ ክኒኖችን በምትወስድበት ግዜ ካልታየ የእርግዝና ምልክት ሊሆን ይችላል። በተለይ ይህ የሚሆነው መድሀኒቱን በየእለቱ መዋጥ የማይቻልበት አጋጣሚ ሲፈጠር ወይም ሲረሳ ነው። ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት እንደጸነሰች ከጠረጠረች ወደሀኪም ሄዳ ማረጋገጥ አለባት። ነገር ግን ለሁለት ወር ይህ ደም ካልታየ እና መድሀኒቱን በሚገባ በየእለቱ የምትውጥ ከሆነ ያልተጠበቀ እርግዝና ይሆናል ብላ መፍራት የለባትም።
ላልተጠበቀ እርግዝና ላለመጋለጥ
- መድሀኒቱን መውሰድ ከጀመሩ አንስቶ ለሚከተሉት ሰባት ቀኖች ሌላ ተጨማሪ የወሊድ መከላከያ (ለምሳሌ ኮንዶም) መጠቅም ይመከራል።። በተለይ የመጀመሪያው ቢጫ ክኒን የወር አበባ በታየበት የመጀምሪያ ቀን ካልተወሰደ ይህ መድሀኒት ለመጀምሪያዎቹ ሰባት ቀኖች ከእርግዝና አይከላከልም።
- መድሀኒቱን የጤና ባለሙያ እንደመከረዎ ሳይረሱ በየእለቱ በተመሳሳይ ሰአት ይውሰዱ።
- የጤና መታወክ በሚኖርበት ግዜ አንድ ሴት ይህን መድሀኒት ከወሰደች እስከ ሶስት ሰአት ባለው ግዜ ውስጥ ካስመለሳት የቀኑን ክኒን እንዳልዋጠች መቁጠር አለባት። እንዲህ ባለው ግዜ ተጨማሪ የወሊድ መቆጣጠሪያ (ለምሳሌ ኮንዶም) መጠቀም አስፈላጊ ነው።
መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?
ይህ መድሀኒት የሚሰራው በየእለቱ በተመሳሳይ ሰአት ከተወሰደ ነው። ነገር ግን ክኒኑን ለመውሰድ የማይቻልበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ወይም መዋጥ ከረሱ የሚከተለውን ያንብቡና ጥንቃቄ ያድርጉ
- አንድ ቢጫ ክኒን መዋጥ ከረሱ
- እንዳስታወሱ የረሱትን ክኒን ይዋጡ።
- የሚቀጥለውን ክኒን በሰአቱ ይዋጡ። ተጨማሪ የእርግዝና መከላከላከያ መጠቀም አስፈላጊ አይደለም።
- ቢጫ ክኒን በሚውጡበት የመጀመሪያ ወይም ሁለተኛ ሳምንት ውስጥ ለተከታታይ ሁለት ቀን ክኒን መዋጥ ከረሱ
- እንዳስታወሱ ሁለት ክኒን ይዋጡ። በሚቀጥለው ቀን የሚቀጥሉትን ሁለት ክኒኖች ይዋጡ።
- ከዚህ በሁዋላ በተለመደው ሰአት አንድ ክኒን በየእለቱ ይዋጡ።
- ሁለት ቢጫ ክኒን መዋጥ ከረሱበት ቀን አንስቶ ለሚቀጥሉት ሰባት ቀኖች እርግዝና ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህም ተጨማሪ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል።
- ቢጫ ክኒን በሚውጡበት ሶስተኛ ወይም አራተኛ ሳምንት ውስጥ ለተከታታይ ሁለት ቀን ክኒን መዋጥ ከረሱ
- መድሀኒቱን የጀመሩት የወር አበባ በታየበት የመጀመሪያው ቀን ከሆነ
- የቀረዎትን ወራዊ ክኒኖች ይጣሉ።
- እንደአዲስ (ከአዲስ ብሊስተር ካርድ) አንድ ቢጫ ክኒን በተለመደው ሰአት በመውሰድ ይጀምሩ።
- መድሀኒቱን የጀመሩት የወር አበባ በታየበት የመጀምሪያው እሁድ ቀን ከሆነ
- መድሀኒቱን ከረሱበት ቀን አስቶ እስከሚቀጥለው እሁድ ድረስ የቀረውን ክኒን በቀን አንድ ይዋጡ።
- እሁድ ሲደርስ የቀረውን ወራዊ ክኒኖች ይጣሉ እና እንደአዲስ (ከአዲስ ብሊስተር ካርድ) አንድ ቢጫ ክኒን በተለመደው ሰአት በመውሰድ ይጀምሩ።
- ሁለት ቢጫ ክኒን መዋጥ ከረሱበት ቀን አንስቶ ለሚቀጥሉት ሰባት ቀኖች እርግዝና ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህም ተጨማሪ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል።
- መድሀኒቱን የጀመሩት የወር አበባ በታየበት የመጀመሪያው ቀን ከሆነ
- በየትኛውም ሳምንት ውስጥ ሶስት ቢጫ ክኒኖችን መዋጥ ከረሱ
- መድሀኒቱን የጀመሩት የወር አበባ በታየበት የመጀመሪያው ቀን ከሆነ
- የቀረዎትን ወራዊ ክኒኖች ይጣሉ።
- እንደአዲስ (ከአዲስ ብሊስተር ካርድ) አንድ ቢጫ ክኒን በተለመደው ሰአት በመውሰድ ይጀምሩ።
- መድሀኒቱን የጀመሩት የወር አበባ በታየበት የመጀምሪያው እሁድ ቀን ከሆን
- መድሀኒቱን ከረሱበት ቀን አስቶ እስከሚቀጥለው እሁድ ድረስ የቀረውን ክኒን በቀን አንድ ይዋጡ።
- እሁድ ሲደርስ የቀረውን ወራዊ ክኒኖች ይጣሉ እና እንደአዲስ (ከአዲስ ብሊስተር ካርድ) አንድ ቢጫ ክኒን በተለመደው ሰአት በመውሰድ ይጀምሩ።
- ሁለት ቢጫ ክኒን መዋጥ ከረሱበት ቀን አንስቶ ለሚቀጥሉት ሰባት ቀኖች እርግዝና ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህም ተጨማሪ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል።
- ለተከታታይ ሁለት ወሮች የወር አበባ ካላዩ የእርግዝና ምልክት ሊሆን ስለሚችል ወደሀኪም ቤት ሄደው ያረጋግጡ።
- መድሀኒቱን የጀመሩት የወር አበባ በታየበት የመጀመሪያው ቀን ከሆነ
- ሰባቱን ነጭ ክኒኖች በሚወስዱበት ቀኖች ክኒን መዋጥ ከረሱ
- የረሱትን ክኒን ይጣሉ።
- የሚቀጥለውን ክኒን በተለመደው ሰአት ይዋጡ።
- ተጨማሪ የእርግዝና መከላከላከያ መጠቀም አስፈላጊ አይደለም።
ምን ያህል ቀኖች መዋጥ እንደረሱ ከዘነጉ ወይም ምን ማድረግ እንዳለብዎት እርግጠኛ ካልሆኑ ለጤና ባለሙያ ያማክሩ።
በዚህ መድሃኒት ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች (Side effects)
ይህን መድሀኒት የሚወስዱ አንዳንድ ሴቶች የሚከተሉት የጤና እክሎች ሊገጥማቸው ይችላል፦
- የወር አበባ ግዜ የሚታይ አይነት ህመም
- ራስምታት
- የጡት ህመም
- ማቅለሽለሽ/ማስመለስ
- የሆድ ህመም
- የመደበት ስሜት
- የወር አበባ መቅረት መቀነስ ወይም መጨመር
- የሰውነት ማሳከክ
- ብጉር
- ማድያት (Melasma)
- የእግር ማበጥ
- የአይን ህመም
- የሰውነት ክብደት መጨመር
- የወገብ ህመም
- ያልተለመደ ቢሆንም ክኒን ካቆሙ በሁዋላ ለጥቂት ግዜ ለመጸነስ አለመቻል በአንዳንድ ሴቶች ላይ ታይቷል።
እነዚህ ምልክቶች መድሀኒቱን ሰውነትዎ ሲላመደው የማይቀንስ ከሆነ ወይም ምልክቶቹ ከሚችሉት በላይ ከሆነ ለሀኪምዎ ይንገሩ።
በተጨማሪም በዚህ መድሀኒት ምክንያት የሚከተሉት ህመሞች በጥቂት ሴቶች ላይ ሊከሰት ይችላል።
- ቬን ውስጥ ደም የመጓጎል (Venous thromboemblism) ፦ ይህ ደም መጓጎል የእግር (Deep vein thrombosis) ወይም የሳንባ (pulmonary embolism) ደምስሮች ውስጥ ሊፈጠር ይችላል። ይህን ለመከላከል ይህን መድሀኒት ከመጀምርዎ በፊት ከዚህ በፊት የደም ማቅጠኛ መድሀኒት ይወስዱ ከነበረ ወይም በእናት በአባትዎ እንዲህ አይነት በሽታ ካለ ለሀኪምዎ ይንገሩ።
- የደም ግፊት መጨመር (High blood pressure) ፦ ይህ የሚሆነው በተለይ እድሜ ሲጨምር እና ለረጅም ግዜ ይህን መድሀኒት የተቀመች ሴት ስትሆን ነው። በዚህ ምክንያት የሚመጣን ከፍተኛ ደም ግፊትን ለመከላከል በየግዜው የደም ግፊትን መለካት ይመከራል። ደም ግፊቷ በተተደጋጋሚ ከ 120 በ 80 በላይ ሆኖ ከተገኘ ከሀኪም ጋር በመማከር አስፈላጊ ጥንቃቄ ማድረግ ይቻላል።
ለዚህ መድሃኒት የሃኪም ክትትል ያስፈልገኛል?
ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት ቢያንስ በየአመቱ የሀኪም ክትትል እንድታደርግ ይመከራል። ይህን ማድረግ በዚህ መድሀኒት የተነሳ ሊመጡ የሚችሉ ህመሞች ሳይከቱ በፊት ለማወቅ እና የሚያስፈልገውን ጥንቃቄ ለመውሰድ ይረዳል።
መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ
መድሃኒትዎን፤ ሙቀት እና ቅዝቃዜ የማይበዛበት፤ ደረቅ ቦታ ያስቀምጡ። መድሃኒትን መታጠቢያ ቤት ማስቀመጥ አግባብ አይደለም። ህጻናት እና የቤት እንስሳት የማይደርሱበት ቦታ ያስቀምጡ።
ሌሎች ጥንቃቄዎች
በዚህ መድሀኒት ውስጥ የሚገኘው ፕሮጀስቲን በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን የፓታስየም መጠን እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ይህ የሚያጋጥመው ሌሎች የፓታስየም መጠን የሚጨምር መድሀኒት የሚወስዱ ወይም ህመም ያጋጠማቸው ሴቶች ላይ ነው። ይህ ፓታስየም በሰውነት ውስጥ ከሚያስፈልገው በላይ ሲጨምር ለጤና አደጋ ሊፈጥር ይችላል። ይህን መድሀኒት ሲወስዱ በጤናዎ ላይ ለውጥ ካለ ወይንም አዲስ መድሀኒት ከታዘዘልዎ በአፍ የሚወሰድ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንደሚጠቀሙ ለሀኪምዎ መንገር ያስፈልጋል። ሀኪምዎ ለፓታስየም መጨመር የተጋለጡ መሆንዎን ከገመተ የደም ፓታስየም ለመገምገም ላብራቶሪ ምርመራ ሊያዝልዎ ይችላል።
ፓታስየም ሊጨምሩ የሚችሉ መድሀኒቶች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው
- ስቴሮይድ ነክ ያልሆኑ አንቲኢንፍላማቶሪ መድሀኒቶች (NSAIDs)(ለረጅም ግዜ በተከታታይ ሲወሰዱ)
- አይቢፕሮኦፊን (ibuprofen) ሞትሪን (Motrin) አድቪል (Advil)
- ናፕሮክሲን (Naproxen) አሊቭ (Aleve) እና ሌሎች
- አንዳንድ ውሀ ከሰውነት እንዲወጣ የሚረዱ መድሀኒቶች (Potassium-sparing diuretics)
- ስፓይርኖላክቶን (Spironolactone)
- አምሎራይድ (Amiloride)
- ኢፕልርኖን (Eplerenone)
- ትራይአምተሪን (Triamterene)
- በመድሀኒት መልክ የተዘጋጀ ፓታስየም
- አንጅዮቴንሲን ሁለት ሪሰፕተር አንታጎኒስቶች (Angiotensin-II receptor antagonists)
- ኮዛር (Cozaar)
- ዳዮቫን (Diovan)
- ኤቫፕሮ (Avapro)እና ሌሎች
- አንጂዎቴንሲን ቀያሪ ኢንዛይም ኢንሂቢተሮች (ACE inhibitors)
- ካፖቴን (Capoten)
- ቫሶቴክ (Vasotec)
- ዘስትሪል (Zestril) እና ሌሎች
- ሄፓሪን (Heparin)
- አልደስትሮን አንታጎኒስቶች (Aldosterone antagonists)
ከፍተኛ ጥንቃቄ (Black Box Warning)
ሲጃራ የሚያጨሱ ሴቶች ድሮስፓይርኖን/ኤትናይል ኤስትርዳዮል ሲወስዱ አደገኛ ለሆነ የልብ እና ደምስር በሽታ ይጋለጣሉ። በተለይ እድሜ ሲጨምር ለበሽታው የመጋለጥ እድሉ እየሰፋ ይሄዳል። ከሰላሳ አምስት አመት እድሜ በላይ እና ሲጃራ የሚያጨሱ ከሆኑ ይህን መድሀኒት እንዳይጠቀሙ ኤፍዲኤ (FDA) ያሳስባል።
ማጣቀሻ
- OCELLA 28 TABLETS [package insert]. Wayne, NJ 07470: Bayer HealthCare Pharmaceuticals Inc; 2010.
- YASMIN [package insert]. Wayne, NJ 07470: Bayer HealthCare Pharmaceuticals Inc; 2012.
ቀን: 09/23/20
በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ የዋጋ ቅናሽ ለማግኘት GoodRx ኩፖን ጠቃሚ ነው። ኩፓኑ የሚያሳየው ሂሳብ እንደሚኖሩበት አከባቢ እና ፋርማሲ የተለያየ ሊሆን ይችላል። ኩፖኑን ለማተም ወደ GoodRX ድረገጽ ይሂዱ።
በቅርብ ግዜ የወጡ ጽሁፎች
- የደም ግፊት ምርመራ
የደም ግፊት ምርመራ የሚደረገው በደም ግፊት መለኪያ መሳሪያ ወይም ስፊግሞ-ማኖ-ሜትር( Sphygmomanometer) ነው። ወደሀኪም ቤት ሲሄዱ…
- የደም ግፊት (Hypertension)
የደም ብዛት ለብዙ አመታት ምንም ምልክት ሳያሳይ ህመምተኛውን ሊጎዳ ይችላል። በዚህ ምክንያት አንዳንዴ የደም ብዛት…
- ላይስኖፕሪል (Lisinopril)
ላይስኖፕሪል(Lisinopril) ከፍተኛ ደም ግፊት ለማስተካከል የሚታዘዝ መድሃኒት ነው። እንዲሁም ለሌሎች ህመሞች ሊታዘዝ ይችላል።