የቅደመ ስኳር በሽታ (Pre-Diabetes) ምንድነው?
በደም ውስጥ ያለ ግሉኮስ መጠን ሲጨምር ነገር ግን የስኳር በሽታን ያህል ከፍተኛ ካልሆነ ቅድመ ስኳር በሽታ ወይም ፕሪ ዳያቤቲስ (pre-diabetes) ይባላል። በደም ጉሉኮስ (በባዶ ሆድ) ምርመራ ላይ 100 እስከ 125 ሚሊግራም በዴሲሊትር ወይም በኤዋንሲ(A1C) ምርመራ ከ 5.7% – 6.4% ያሳያል።።
በጤና ላይ የሚያስከትለው ችግር
የደም ግሉኮሱን ካልተቆጣጠረ ቅድመ ስኳር በሽታ ያለበት ሰው ለስኳር በሽታ በከፍተኛ ደረጇ የተጋለጠ ነው። በተለይ ከ60 አመት እድሜ በታች ከሆነ፣ ውፍረት ካለ፣ በርግዝና ግዜ የደም ግሉኮስ ከፍተኛ ከነበረ ወደስኳር በሽታ የመለወጥ እድሉ ከፍተኛ ነው።
በምርመራ ይህ የታወቀለት ሰው እራሱን እንደ እድለኛ መቁጠር ይችላል። ምክንያቱም ህመሙ ከፍቶ በስኳር በሽታ ሰበብ የሚመጡ በሽታዎች ሳይከሰቱ በፊት የጤናውን ሁኔታ ማወቅ ችሏል። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ፤ አመጋገቡን በማስተካከል፤ የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ፣ የሃኪሙን ምክር በመከተል ቅድመ ስኳር በሽታ ወደ ስኳር በሽታ እንዳይሄድ ለማድረግ እድል አለው።
ምልክቶች
በዚህ ደረጃ ላይ እያለ ህመምተኛው ምንም ምልክት ላያሳይ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች አንገታቸው፣ ብብታቸው፣ ጉልበታቸው፣ ክርናቸው፣ ወይም የጣታቸው መተጣጠፊያ ላይ የሚገኝ ቆዳቸው በተለየ መልኩ ይጠቁራል። ይህ ጥቁረት አንዳንዴ እድፍ ይመስላል። ነገር ግን እንደእድፍ በመታጠብ አይለቅም። ከዚህ ውጭ የማይረካ የውሃ ጥም፣ ቶሎ ቶሎ የረሃብ ስሜት ሲሰማዎ፣ እና አሁንም አሁንም የውሃ ሽንት የሚለዎ ከሆነ ህመሙ ወደስኳር በሽታ መለወጡን ጠርጥረው ለሃኪም ማማከር ተገቢ ነው።
ለመከላከል
ቅድመ ስኳር በሽታን ለመከላከል የሚረዱ እርምጃዎች ቅድመ ስኳር በሽታ ወደ ስኳር በሽታ እንዳይሄድ ከሚረዱት ጋር ተመሳሳይ ናቸው። እነዚህም፣ የተመጣጠነ ጤናማ ምግብ መመገብ፣ በሳምንት ቢያንስ 150 ደቂቃ (በየእለቱ ቢያንስ ሃያ ደቂቃ) እንደሩጫ ያለ ስፓርት መስራት፣ ውፍረት መቀነስ፣ የሚያጨሱ ከሆነ መተው፣ እንዲሁም ከፍተኛ የደምግፊት ወይም ኮሌስትሮል ካለብዎ ህክምና መከታተል ናቸው።
ህክምና
የቅድመ ስኳር በሽታ ያለበት ሰው፤ እንደዶክተሩ ምክር የደም ግሉኮሱን በየግዜው መታየት አለበት። የደም ግፊት ወይም እና ኮሌስትሮል ካለ በቂ ህክምና ማድረግ ለህመምተኛው ጤና ይመከራል። አንዳንድ ዶክተሮች የህመምተኛውን አጠቃላይ ጤና በማየት ሜትፎርሚን የተባለ ክኒን ያዛሉ። ይህ መድሃኒት የስኳር በሽታን ለማዘግየት እንዲሁም የደም ግሉኮስን ለመቀነስ ለብዙ ስኳር በሽተኞች ይታዘዛል። ምንም መድሃኒት ባይታዘዝ እንኳን አመጋገብ መለወጥ እና የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ለወደፊቱ ጤንነትዎ አስፈላጊ መሆኑን አይዘንጉ።
በቅርብ ግዜ የወጡ ጽሁፎች
- ስኳር በሽታ
የስኳር በሽታ በደም ውስጥ ከመጠን በላይ ግሉኮስ ሲኖር የሚፈጠር በሽታ ነው። የዚህ መንስኤ በተፈጥሮ ከጣፊያ…
- ሜትፎርሚን (Metformin HCL)
ሜትፎርሚን፤ ስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች፤ በደማቸው ያለውን የግሉኮስ መጠን በአግባቡ ለመቀነስ የሚታዘዝ መድሃኒት ነው።
1 thought on “ቅድመ ስኳር በሽታ (Pre-diabetes)”
Comments are closed.