የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ ሲታግልፕቲን (Sitagliptin)
ብራንድ ስም፦ ጅኑቪያ (Januvia)
ምድብ፦ ዲፒፒ 4 የሚያግድ (DPP-4 Inhibiter)
ሲታግልፕቲን ለምን ይታዘዛል?
በአይነት ሁለት የስኳር በሽታ ህመምተኞች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል ይረዳል።
ሲታግልፕቲን በምን መልኩ ይመረታል?
ሲታግልፕቲን በአፍ የሚዋጥ ኪኒን ነው። ብዙ ጊዜ በ100፣ 50፣ እና 25 ሚሊግራም መጠን ይመረታል።
ሳክስግልፕቲን እንዴት ነው የሚሰራው?
አንድ ሰው ምግብ ሲበላ ወይም የደም ግሉኮሱ ከፍ ሲል ኢንክሪቲን የሚባሉ ሆርሞኖች አንጀት አከባቢ ይመነጫሉ። ኢንክሪቲኖች በጣፊያ ውስጥ የኢንሱሊን ምርት እንዲጨምር እንዲሁም የግሉካጎን ምርት እንዲቀንስ ምልክት ይሰጡታል። የኢንሱሊን መጠን መጨመር በደም ያለውን የግሉኮስ መጠን ይቀንሳል። በአንጻሩ ከጣፊያ የሚመረተው እና የሚመነጨው የግሉካጎን መጠን መቀነስ በጉበት ውስጥ ተከማችቶ የሚቀመጠውን ግላይኮጅን ወደግሉኮስ ተለውጦ ወደደም ዝውውር እንዳይገባ ያደርገዋል። ስለዚህ የኢንሱሊንን ምርት በመቆጣጠር ኢንክሪቲኖች የደም ግሉኮስን ይቀንሳሉ። የደም ግሉኮስ የሚፈለገውን ያህል ዝቅ ካለ በኋላ ዲፒፒ 4 የሚባሉ ኢንዛይሞች ኢንክሪቲን በሚገኝበት የአንጀት አከባቢ ይመነጫሉ። ኢንክሪቲኖችን በመሰባበር ለጣፊያ የሚሰጡትን ምልክት እንዲያቆም ያደርጋሉ።
ይህ መድሀኒት ዲፒፒ 4 ኢንዛይሞች ኢንክሪቲኖችንን እንዳይሰባብሩ በማድረግ ኢንክሪቲኖች ለረጅም ግዜ በሰውነት እንዲቆዩ ያደርጋል። ኢንክሪቲኖች ለረጅም ግዜ በሰውነት መቆየት የኢንሱሊን ምርት እንዲቀጥልና የግሉካጎን ምርት እንደቀነሰ እንዲቆይ ያደርጋሉ። የዚህ አጠቃላይ ውጤት በደም ውስጥ የሚገኘው የግሉኮስ መጠን ማስተካከል ይሆናል።
የሲታግልፕቲን አወሳሰድ
- የሀኪም ትእዛዝ ይከተሉ።
- ብዙ ግዜ በቀን አንድ ግዜ ይወሰዳል።
- መድሀኒቱ የሚወሰድበት ሰአት ተመሳሳይ ቢሆን ይመረጣል።
- ከምግብ ጋር ወይም ያለምግብ ብቻውን መውሰድ ይቻላል።
መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?
ወድያው እንዳስታወሱ ይውሰዱ። ብዙ ሰአት ካለፈ ግን ይተውት እና በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ጊዜ የተለመደውን መጠን ይዋጡ። የረሱትን ጨምረው ለመዋጥ አይሞክሩ።
የመድሀኒቱ የጎን ጉዳት (Side-effect)
ይህን መድሀኒት የሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች ላይ እነዚህ የህመም ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ
- እንደጉንፋን (Nasopharyngitis) ያለ ህመም (ከአፍንጫ የሚወጣ ፈሳሽ(ንፍጥ)፣ የአፍንጫ መደፈን፣ የጉሮሮ ህመም)
- ራስምታት
ይህ ብዙ ግዜ መድሀኒቱ ሲጀመር አከባቢ የሚሰማ ህመም ነው። መድሀኒቱ ከሰውነት ጋር ሲላመድ ይተዋል። ካልተወ ወይም ከአቅም በላይ ከሆነ ግን ለሀኪም ያማክሩ።
ለዚህ መድሃኒት የሃኪም ክትትል ያስፈልገኛል?
የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሀኪም ክትትል ያስፈልጋቸዋል። ይህም የሚደረገው
- የታዘዘላቸው መድሀኒት የደም ግሉኮሳቸውን በመቆጣጠር ያመጣውን ውጤት ለማወቅ
- በመድሀኒቱ ምክንያት የሚመጣ የጎን ጉዳት ካለ ለማወቅ
- በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጣ ሌላ ህመም (ለምሳሌ የኩላሊት በሽታ) ካለ በጊዜ ለማወቅ እና የሚያስፈልገውን ህክምና ለማድረግ ነው።
ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ምንድነው?
ይህ መድሀኒት የሚሰራው ሀኪም ባዘዘው መሰረት በየእለቱ ሲወሰድ ነው።
ከመድሀኒቱ በተጨማሪ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግና አመጋገብ ማስተካከል የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋፆ አለው።
ይህ መድሀኒት የደም ግሉኮስን ያስተካክላል እንጂ የስኳር በሽታን አይፈውስም። የስኳር በሽታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ህመም ነው። የህክምናው አላማ የደም ግሉኮስን በመቀነስ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ ኩላሊት እና አይን) ላይ የሚያደርሰውን በሽታ መከላከል ነው። የደም ግሉኮስ ሲቀንስ ይህን መድሀኒት መውሰድ ማቆም የደም ግሉኮስ ተመልሶ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ የደም ግሉኮስ ቢስተካከል ወይም ጤንነት ቢሰማ እንኳን ይህን መድሀኒት ያለሀኪም ትእዛዝ ማቋረጥ አይመከርም።
ሲታግልፕቲን የማይታዘዝላቸው ሰዎች (Contraindication and limitations)
- ከዚህ በፊት ይህን መድሀኒት ወስደው አደገኛ አለርጂ ያጋጠማቸው ሰዎች
- አይነት አንድ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች እንዲሁም
- ከስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ ኪቶአሲዶሲስ (diabetic ketoacidosis) ያጋጠማቸው ሰዎች።
የመድሀኒቱ መስተጋብር (Drug Interaction)
መድሀኒቶች፦ሲታግልፕቲን ዲጃክስን (digoxin/Lanoxin) ከሚባል መደሀኒት ጋር አንድ ላይ ሲወሰድ የዲጃክስን መጠን በሰውነት ውስጥ ሊጨምር ይችላል። ስለዚህ ሁለቱን መድሀኒት የሚወስዱ ሰዎች የሀኪም ክትትል ያስፈልጋቸዋል።
እርጉዝ ሴቶች፦ ይህ መድሀኒት በእርግዝና ግዜ ከእናት ወደፅንስ ሊተላለፍ ይችላል። በእርግዝና ግዜ የስኳር በሽታን መቆጣጠር ለእናትም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት ማርገዟን ስታውቅ መድሀኒቱን ላዘዘላት ሀኪም እንድታሳውቅ ይመከራል።
የሚያጠቡ ሴቶች፦ ሲታግልፕቲን የምትወስድ እናት የጡት ወተት ውስጥ መድሃኒቱ ሊኖር ይችላል። የሚያጠቡ ሴቶች ይህን መድሀኒት ሲወስዱ ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ ሀኪማቸውን ያማክሩ።
ምግቦች፦ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ ጣፋጭ የሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ ካርቦሀይድሬት (carbohydrate) ያላቸውን ምግቦች (ለምሳሌ ዳቦ፣ ፓስታ፣ ጣፋጭ ፍራፍሬዎ) ይቀንሱ። ለስኳር በሽታ ተስማሚ የሆነ የአመጋገብ መከተል ለመድሀኒቱ መስራት እና ለአጠቃላይ ጤንነት ጥሩ ነው።
ሌሎች ጥንቃቄዎች
የኩላሊት በሽታ ሲኖር የሚወስዱት የመድሀኒት መጠን ሊቀነስ ይችላል። ይህን ለማወቅ በየግዜው የኩላሊት ምርመራ ሊታዘዝ ይችላል።
ይህ መድሀኒት የጣፊያ ህመም (pancreatitis) ሊያባብስ ይችላል። የዚህ ህመም ምልክቶች ሀይለኛ የማያቋርጥ እና እስከጀርባ ድረስ የሚሰማ የሆድ ህመም ማቅለሽለሽ ማስታወክ እና ዘይት ያለበት የሚመስል ሰገራ ሊሆን ይችላል። ይህን መድሀኒት እየወሰደ እንዲህ ያለ ህመም የሚሰማው ሰው ለሀኪሙ እንዲያሳውቅ ይመከራል።
በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች መድሀኒቶችን የወሰዱ ጥቂት ሰዎች ላይ የልብ ድካም (heart failure) ታይቷል። ይህንን መድሀኒት ሲወስዱ የልብ ድካም ምልክቶችን ማወቅ ጥሩ ነው። የትንፋሽ ማጠር (በተለይ ጋደም ሲሉ የሚብስ)፣ ያልተለመደ የድካም ስሜት፣ የእግር ወይም የእጅ ማበጥ፣ የሰውነት ክብደት በፍጥነት መጨመር፣ ደረት ላይ ህመም መኖር ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ምልክቶች ከታዩ ለሀኪምዎ ይንገሩ።
ይህን መድሀኒት ሲወስዱ የመገጣጠሚያ ህመም (joint pain) ሊሰማ ይችላል። እንዲህ አይነት ህመም ካጋጠመ ለሀኪም ማማከር ጥሩ ነው።
አንዳንድ ሰዎች ለዚህ መድሀኒት አደገኛ አለርጂ ሊኖራቸው ይችላል። አናፍላክሲስ (Anaphylaxis)፣ አንጂዮኢዴማ (Angioedema)፣ እና ስቲቨን ጆንሰን (Stevens-Johnson Syndrom) አጣዳፊ ህክምና የሚያስፈልጋቸው አለርጂ አይነቶች ናቸው። እነዚህ የህመም ምልክቶች መካከል አንዱ ከታየ ቶሎ ሀኪም ጋር መሄድ አስፈላጊ ነው። ዋና ዋና ምልክቶች
- ለመተንፈስ መቸገር
- የፊት የምላስ የከንፈር ወይም የጉሮሮ ማበጥ
- የቆዳ ሽፍታ እና ማሳከክ
- የቆዳ መቅላት
- ውሃ የሚቋጥር ሽፍታ
- የቆዳ መሰነጣጠቅ ሊሆን ይችላሉ።
ይህ መድሀኒት ብቻውን ሲወሰድ ዝቅተኛ የደም ግሉኮስ (hypoglycemia) አያመጣም ማለት ይቻላል። ነገር ግን ከሌሎች የስኳር በሽታ መድሀኒቶች ጋር እንደተጨማሪ ሊወሰድ ይችላል። በዚህ ግዜ የዝቅተኛ የደም ግሉኮስ ምልክቶችን እንዲሁም መወሰድ ያለበትን ጥንቃቄ ማወቅ ያስፈልጋል።
ሀይፓግላይስሚያ (Hypoglycemia)
የደም ግሉኮስ ሲለካ ከ70 በታች ሲሆን ወይም አንዳንድ የህመም ምልክቶች ሲታዩ የደም ግሉኮስ ከሚፈለገው በታች ነው (Hypoglycemia) ይባላል። እንደከፍተኛ የደም ግሉኮስ ሁሉ ይህ የደም ግሉኮስ በጣም ዝቅ ማለት ለጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል።
ይህን የጎን ጉዳት ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮች ውስጥ መድሀኒቱን ያለምግብ መውሰድ፣ በቂ ምግብ አለመመገብ፣ እና ሌሎች አንዳንድ መድሀኒቶች ናቸው። እንዲሁም ከ65 አመት በላይ እድሜ ያላቸው ሰዎች ለዚህ ጎን ጉዳት የበለጠ የተጋለጡ ናቸው። ምልክቶቹን ማወቅ እና ጥንቃቄ ማድረግ ጥሩ ነው።
ዋና ዋና የህመም ምልክቶች
- የረሀብ ስሜት
- የመንቀጥቀጥ ስሜት
- በላብ መጠመቅ
- ብዥታ
- የሰውነት መዛል
- ያለተለመደ ግራ መጋባት (confusion)
- ራስ ማዞር
- የልብ በሀይል መምታት፣
- እንዲሁም ከባሰ እራስን መሳት ናቸው።
እነዚህ ምልክቶች የተሰማው ሰው የሚከተሉትን ማድረግ አለበት
- ከተቻለ የደም ግልሉኮስ መለካት
- ይህ ካልተቻለ ወይም ተለክቶ የደም ግልኮስ ከ70 በታች ከሆነ ስኳርነት ያለው ምግብ ወይም መጠጥ መውሰድ። ለምሳሌ የግሉኮስ ታብሌት፣ አንድ ማንኪያ ስኳር፣ ማር፣ ከረሜላ፣ ግማሽ ብርጭቆ የብርቱካን ጭማቂ ወይም አንድ ብርጭቆ ወተት መውሰድ ይቻላል።
- ከ15 ደቂቃ በሁዋላ የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ደግሞ መለካት።
- ተለክተው ከ70 በላይ ከሆነ ቀለል ያለ ምግብ መመገብ
- ተለክተው ከ70 በታች ከሆነ ከ 1 –3 ያሉትን የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ እስኪሆን ድረስ መደጋገም።
- የስኳር በሽታዎን ለሚከታተል ሀኪምዎ መንገር አይርሱ።
መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ
ይህ መድሀኒት ሙቀት፣ ቅዝቃዜ እና እርጥበት በሌለበት ህጻናት በማይደርሱበት ቦታ መቀመጥ አለበት።
ኩፓኖች
ይህ መድሀኒት ከሌሎች መድሀኒቶች ሲወዳደር ውድ ነው
የአምራቹ ኩፓን
የጅንቪያ አምራች ለተጠቃሚዎች እስከ 150 ዶላር ድረስ ለ 12 ወር(አንድ አመት) ቅናሽ ይሰጣል። ይህንን ቅናሽ ለማግኘት በአምራቹ ዌብሳይት ማመልከቻ መሙላት ያስፈልጋል። ይህን ኩፓን የምሰጠው ከአሜሪካ (USA) ብቻ ለሚመጡ የመድሀኒት ማዘዣዎች ነው። ታካሚው መንግስታዊ ያልሆነ ኢንሹራንስ ሊኖረው ይገባል። የመንግስት ኢንሹራንስ ምሳሌዎች ሜድኬር (Medicare) እና ትራይኬር (Tricare) ናቸው።
ማጣቀሻ
- “Diabetes Mellitus.” Pharmacotherapy Handbook, by Barbara G. Wells et al., McGraw-Hill Education, 2017, pp. 161–175.
- JANUVIA® (sitagliptin) Tablets [package insert]. Whitehouse Station, NJ 08889, USA: Merck & Co., Inc.; 2019.
- Tseng, Chin-Hsiao. “Sitagliptin and heart failure hospitalization in patients with type 2 diabetes.” Oncotarget vol. 7,38 (2016): 62687-62696. doi:10.18632/oncotarget.10507
ቀን
01/23/21
በቅርብ ግዜ የወጡ ጽሁፎች
- ሳክስግልፕቲን
ሳክስግልፕቲን በስኳር በሽታ ህመምተኞች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል ይረዳል። አንድ ሰው ምግብ ሲበላ…
- ስኳር በሽታ
የስኳር በሽታ በደም ውስጥ ከመጠን በላይ ግሉኮስ ሲኖር የሚፈጠር በሽታ ነው። የዚህ መንስኤ በተፈጥሮ ከጣፊያ…
- ግልፕዛይድ (Glipizide)
ግልፕዛይድ እነዚህን የተዳከሙ እንዲሁም ጤናማ የጣፊያ ህዋሶች የተሻለ መጠን ያለው ኢንሱሊን እንዲያመርቱ ያደርጋቸዋል። ይህ ኢንሱሊን…