Amharic Health Information

ግልምፕራይድ (Glimepiride)

የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ ግልምፕራይድ (Glimepiride)

ምድብ፦ሰልፎንይልዩርያ (Sulfonylurea)

የብራንድ ስም አማሪል (Amaryl)

ግልምፕራይድ ለምን ይታዘዛል?

በአይነት ሁለት ስኳር በሽታ ህመምተኞች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል ይረዳል።

ግልምፕራይድ በምን መልኩ ይመረታል?

ግልምፕራይድ በአፍ የሚዋጥ ኪኒን ነው። በ 1 በ 2 እና በ 4 ሚግ (mg) ክኒን መጠን ይመረታል።            

ግልምፕራይድ እንዴት ነው የሚሰራው?

አይነት ሁለት የስኳር በሽታ ያለበት ሰው ኢንሱሊን የሚያመርተው የጣፍያ ህዋሶቹ (beta cells of pancreatic islet) ይደክማሉ። እነዚህ ህዋሶች ኢንሱሊን የማምረት አቅማቸው ዝቅተኛ ይሆናል። ኢንሱሊን ከሌለ በደም ውስጥ ያለው ግሉኮስ ወደሚያስፈልገው የሰውነት ክፍል መሄድ አይችልም። በዚህ ምክንያት በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን እየተጠራቀመ እና እየጨመረ ይሄዳል።

ግልምፕራይድ እነዚህን የተዳከሙ እንዲሁም የተቀሩትን ጤናማ የጣፊያ ህዋሶች የተሻለ መጠን ያለው ኢንሱሊን እንዲያመርቱ ያደርጋቸዋል። ይህ ኢንሱሊን በደም ውስጥ ያለው ግሉኮስ ወደሚያስፈልገው የሰውነት ክፍል ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የደም ግሉኮስ መጠንን እንዲቀንስ ያደርጋል።

ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ምንድነው?

ይህ መድሀኒት የሚሰራው ሀኪም ባዘዘው መሰረት በየእለቱ ሲወሰድ ነው።

ከመድሀኒቱ በተጨማሪ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እና አመጋገብ ማስተካከል የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋፆ አለው።

ይህ መድሀኒት የደም ግሉኮስን ያስተካክላል እንጂ የስኳር በሽታን አይፈውስም። የስኳር በሽታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ህመም ነው። የህክምናው አላማ የደም ግሉኮስን በመቀነስ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ ኩላሊት እና አይን) ላይ የሚያደርሰውን በሽታ መከላከል ነው። የደም ግሉኮስ ሲቀንስ ይህን መድሀኒት መውሰድ ማቆም የደም ግሉኮስ ተመልሶ እንዲጨምር ሊያደርገው ይችላል። ስለዚህ የደም ግሉኮስ ቢስተካከል ወይም ጤንነት ቢሰማ እንኳን ይህን መድሀኒት ያለሀኪም ምክር ማቆም ትክክል አይደለም።

የመድሀኒት መስተጋብር

መድሀኒቶች፦  እንዳንድ መድሀኒቶች ከግልምፕራይድ ጋር ሲወሰዱ የጎን ጉዳቱን ሊያባብሱት እንዲሁም የመድሀኒቱ እንዳይሰራ ሊያደርጉት ይችላሉ። ከነዚህም መካከል ያለሀኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ የህመም ማስታገሻዎች አድቪል (Advil) እና አሊቭ (Aleve) ይገኙበታል። ግልምፕራይድ እየወሰዱ አዲስ መድሀኒት ሲጀምሩ ሀኪም ወይም ፋርማሲስት በማማከር ለጎን ጉዳት (side effect) እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ ያድርጉ።

ምግቦች፦ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ ጣፋጭ የሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ ካርቦሀይድሬት (carbohydrate) ያላቸውን ምግቦች (ለምሳሌ ዳቦ፣ ፓስታ፣ ጣፋጭ ፍራፍሬዎ) ይቀንሱ። ለስኳር በሽታ ተስማሚ የሆነ የአመጋገብ መከተል ለመድሀኒቱ መስራት እና ለአጠቃላይ ጤንነት ጥሩ ነው።

አልኮል፦ እንደብዙ መድሀኒቶች ሁሉ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ አልኮል መጠጥ መጠጣት አይመከርም።

እርጉዝ ሴቶች፦ ይህ መድሀኒት በእርግዝና ግዜ ከእናት ወደጽንስ ሊተላለፍ ይችላል። ነገር ግን ይህ መድሀኒት በፅንስ ላይ ጉዳት ማድረሱን ለማወቅ የሚያስችል ሰፊ ጥናት የለም። በእርግዝና ግዜ የስኳር በሽታን መቆጣጠር ለእናትም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት አስፈላጊ ነው። ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት መፀነሷን ስታውቅ መድሀኒቱን ላዘዘላት ሀኪም እንድታሳውቅ ይመከራል።

የሚያጠቡ ሴቶች፦ በእንስሣት ላይ በተደረገ ጥናት መሰረት ግልምፕራይድ የምትወስድ እናት ጡት ወተት ውስጥ መድሃኒቱ ሊኖር ይችላል። በሰዎች ላይ ይህ መድሀኒት በጡት ወተት እንዳለ ወይም እንደሌለ አይታወቅም(1)።  ስለአማራጭ መድሀኒቶች ወይም ማድረግ ስላለብዎት ጥንቃቄ ሀኪምዎን ያማክሩ።

ይህ መድሀኒት የማይታዘዝላቸው ሰዎች (Contraindication)

  1. ከዚህ በፊት ይህን መድሀኒት ወስደው አደገኛ አለርጂ ያጋጠማቸው ሰዎች።
  2. ከስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ ኪቶአሲዶሲስ (diabetic ketoacidosis) ያጋጠማቸው ሰዎች።

የግልምፕራይድ አወሳሰድ

የሀኪም ትእዛዝ ይከተሉ።

በቀን የመጀመሪያው የመብል ሰአት ላይ ከምግብ ጋር መውሰድ ይቻላል።

መድሀኒቱን የሚወሰድበት ሰአት ተመሳሳይ ቢሆን ይመረጣል።

መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?

ወድያው እንዳስታወሱ ይውሰዱ። ብዙ ሰአት ካለፈ ይተውት እና በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ጊዜ የተለመደውን መጠን ይዋጡ። የረሱትን ጨምረው ለመዋጥ አይሞክሩ። ለሀኪምዎ ሳያማክሩ ድንገት መድሃኒትዎን መውሰድ አያቁሙ።

የጎን ጉዳት (Side-effect)

ይህን መድሀኒት የሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች የማዞር ስሜት፣ ድካም፣ የራስ ምታት እና ማቅለሽለሽ ሊሰማቸው ይችላል። ሌሎች ሊታዩ የሚችሉ የጎን ጉዳቶች ቆዳ ማሳከክ፣ ሽፍታ እና የአይን ብዥታ ሊሆን ይችላል።  ብዙ ግዜ እነዚህ ምልክቶች መድሀኒቱን መውሰድ ሲጀምሩ የሚታዩ እና ሰውነት ሲላመድ የሚጠፉ ናቸው። መድሀኒቱን ከዋጡ በሁዋላ ምግብ መብላት ሊረዳ ይችላል። የማይተዎት እና ከአቅም በላይ ከሆነ ለሃኪም ያማክሩ።

ይህን መድሀኒት ሲወስዱ የሰውነት ክብደት መጨመር ሊታይ ይችላል።

ስለሀይፖግላይስሚያ (Hypoglycemia) “ሌሎች ጥንቃቄዎች” በሚለው ርዕስ ስር ያንብቡ።

ለዚህ መድሃኒት የሃኪም ክትትል ያስፈልገኛል?

የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሀኪም ቤት ቀጠሮ መከታተል ያስፈልጋቸዋል። ይህን የሚደረገው

  1. የታዘዘላቸው መድሀኒት ስኳር በሽታቸውን ለመቆጣጠር እየረዳቸው መሆኑን ለማወቅ
  2. በመድሀኒቱ ምክንያት የሚመጡ የጎን ጉዳቶች እየተባባሱ እንዳልሆኑ ለማወቅ
  3. በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጡ ሌሎች ህመሞች (ለምሳሌ የኩላሊት በሽታ) ካሉ በጊዜ ለማወቅ እና የሚያስፈልገውን ህክምና ለማድረግ ነው።

በተጨማሪ የአይነቱ ሁለት የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከጊዜ በሁዋላ ጣፊያቸው ሙሉ በሙሉ ኢንሱሊን የማምረት ችሎታውን ሊያጣ ይችላል። በዚህ ጊዜ ይህ መድሀኒት አይሰራም። ይህን በምርመራ አረጋግጦ ሃኪማቸው ከግልምፕራይድ ወደሌላ መድሀኒት ሊለውጥላቸው ይችላል። ስለዚህ የህክምና ቀጠሮ መከታተል ጥሩ ነው።

ሌሎች ጥንቃቄዎች

መጀመሪያ የሚታዘዘው መድሀኒት መጠን የደም ግሉኮስን ወይም ኤዋንሲን (A1C) ላያስተካክል ይችላል። ስለዚህ ሀኪም ይህን መድሀኒት በትንሽ መጠን ጀምሮ ቀስ በቀስ እየጨመረ መሄድ ይፈልግ ይሆናል።  የስኳር በሽታን መቆጣጠር እስከሚቻል ድረስ የመድሀኒቱ መጠን እያስተካከሉ መሄድ የመድሀኒቱን የጎን ጉዳት (side-effect) ለመቀነስ እና ለህመምተኛው የሚሆነውን ትክክለኛውን የመድሀኒት መጠን ለማግኘት ይጠቅማል።

ሀይፓግላይስሚያ (Hypoglycemia)፦ አንዳንድ ሰዎች ግልምፕራይድ ሲወስዱ የደም ግሉኮሳቸው መጠን ከሚፈለገው በታች ሊወርድ ይችላል።

የደም ግሉኮስ ሲለካ ከ70 በታች ሲሆን ወይም አንዳንድ የህመም ምልክቶች ሲታዩ የደም ግሉኮስ ከሚፈለገው በታች ነው (Hypoglycemia) ይባላል። እንደከፍተኛ የደም ግሉኮስ ሁሉ ይህ የደም ግሉኮስ በጣም ዝቅ ማለት ለጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል።

ይህን የጎን ጉዳት ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮች መድሀኒቱን ያለምግብ መውሰድ፣ በቂ ምግብ አለመመገብ፣ እና ሌሎች አንዳንድ መድሀኒቶች ናቸው።

ዋና ዋና የህመም ምልክቶቹ የረሀብ ስሜት፣ ያለተለመደ ግራ መጋባት (confusion)፣ ራስ ማዞር፣ የሰውነት መዛል፣ የመንቀጥቀጥ ስሜት፣  በላብ መጠመቅ፣ የልብ በሀይል መምታት፣ እንዲሁም ከባሰ እራስን መሳት ናቸው።

እነዚህ ምልክቶች የተሰማው ሰው ማድረግ ያለበት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው

  1. ከተቻለ የደም ግልሉኮስ መለካት
  2. ይህ ካልተቻለ ወይም ተለክቶ የደም ግልኮስ ከ70 በታች ከሆነ ስኳርነት ያለው ምግብ ወይም መጠጥ መውሰድ። ለምሳሌ የግሉኮስ ታብሌት፣ አንድ የሻይ ማንኪያ ስኳር፣ ከረሜላ፣ ግማሽ ብርጭቆ የብርቱካን ጭማቂ ወይም አንድ ብርጭቆ ወተት መውሰድ ይቻላል።
  3. ከ15 ደቂቃ በሁዋላ የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ደግሞ መለካት።
  4. ተለክተው ከ70 በላይ ከሆነ ቀለል ያለ ምግብ መመገብ
  5. ተለክተው አሁንም ከ70 በታች ከሆነ እንደገና ጣፋጭነት ያለው ምግብ መብላት እና ወደሀኪም ቤት መሄድ።
  6. ይህ አንዴ ካጋጠመ የስኳር በሽታዎን ለሚከታተል ሀኪምዎ መንገር አይርሱ።

የልብ ወይም የደም ስር በሽታ ላለበት ሰው ከግልምፕራይድ የተሻለ መድሀኒት ሊኖር ይችላል። መድሀኒት ለሚያዝልዎት ሀኪም ከዚህ በፊት የልብ ወይም የደም ስር በሽታ  አጋጥሞት ከነበረ መንገር አይዘንጉ።

መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ

ይህ መድሀኒት የሚቀመጥበት ቦታ ሙቀት፣ ቅዝቃዜ እና እርጥበት የማይበዛበት ህጻናት የማይደርሱበት ቦታ ነው። 

ማጣቀሻ

  1. Amaryl[package insert]. Bridgewater, NJ 08807: sanofi-aventis U.S. LLC, Inc.; 2009.
  2. American Diabetes Association. 9. Pharmacologic Approaches to Glycemic Treatment: Standards of Medical Care in Brunton, Laurence L., et al. Goodman & Gilman’s the Pharmacological Basis of Therapeutics. 12th ed., McGraw Hill Education, 2011.
  3. Diabetes-2020. Diabetes Care. 2020 Jan;43(Suppl 1):S98-S110. doi: 10.2337/dc20-S009. Erratum in: Diabetes Care. 2020 Aug;43(8):1979. PMID: 31862752.
  4. “Diabetes Mellitus.” Pharmacotherapy Handbook, by Barbara G. Wells et al., McGraw-Hill Education, 2017, pp. 161–175.

ቀን: 01/25/21

ኩፓኖች