የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ ኤክሰናታይድ (Exenatide)
ብራንድ ስም፦ ባይዱርዮን (Bydureon) ባየታ (Byetta)
ምድብ፦ ጂኤልፒ 1 አይነት (GLP-1 Agonist)
ኤሰናታይድ ለምን ይታዘዛል?
ኤሰናታይድ በአይነት ሁለት ስኳር በሽታ ህመምተኞች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል ይረዳል።
ኤሰናታይድ በምን መልኩ ይመረታል?
ኤክሰናታይድ በቆዳ ስር የሚወጋ መርፌ ነው። በሁለት አይነት መልክ ይመረታል። አንደኛው ብራንድ ባይዱርዮን (Bydureon) ሲሆን ሁለተኛው ባየታ (Byetta) ነው። ሁለቱም በውስጣቸው የሚይዙት ኤክሰናታይድ ቢሆንም አጠቃቀማቸው የተለያየ ነው።
1. ባይዱርዮን
- ለአንድ ጊዜ የሚሆን 2 ሚሊግራም ኤክሰንታይድ የሚይዝ የመድሀኒት ብልቃጥ (ቫየል) ይመረታል። በአንድ ካርቶን ውስጥ አራት የመድሀኒት ብልቃጦች ይኖራሉ።
- ለአንድ ጊዜ የሚሆን 2 ሚሊግራም ኤክሰንታይድ የሚይዝ ፔን ይመረታል። በአንድ ካርቶን ውስጥ አራት ፔኖች ይኖራሉ።
2. ባየታ
- በአንድ ጊዜ 5 ማይክሮግራም (5 mcg) በ1.2 ሚሊሊትር ኤክሰናታይድ የሚሰጥ ፔን ይመረታል። አንድ ፔን 60 ጊዜ ለመወጋት ይበቃል።
- በአንድ ጊዜ 10 ማይክሮግራም (10 mcg) በ2.4 ሚሊሊትር ኤክሰናታይድ የሚሰጥ ፔን ይመረታል። አንድ ፔን ለ60 ጊዜ ለመወጋት ይበቃል።
ኤክሰናታይድ እንዴት ነው የሚሰራው?
ኤክሰናታይድ በሰውነት ውስጥ የኢንሱሊንን መጠን በመጨመር እና የግሉካንን መጠን በመቀነስ የደም ግሉኮስን ያስተካክላል።
ኤክሰናታይድ በተፈጥሮ ሰውነት ውስጥ የሚገኘውን ጂኤልፒ -1 ን እንዲመስል ተደርጎ የተሰራ መድሀኒት ነው። ጂኤልፒ 1 በአንጀት ከሚገኙ ኢንክሪቲን ከሚባሉ ሆርሞኖች መካከል አንዱ ሲሆን የሚጠቅመው ምግብ ከተበላ ብኋላ ከፍ ያለ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል ነው። ጂኤልፒ – 1 የሚሰራው በሰውነት ውስጥ ከፍተኛ የግሉኮስ መጠን ሲኖር ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ ጂኤልፒ 1 ቢኖር እንኳን የደም ግልኮስን ዝቅ አያደርግም።
ጂኤልፒ 1 የደም ግሉኮስን የሚቆጣጠረው አንድም ጣፊያ የኢንሱሊን ምርቱን እንዲጨምር በማድረግ እንዲሁም የግሉካጎን ምርቱን እንዲቀንስ በማድረግ ነው። የኢንሱሊን መጠን መጨመር በደም ያለውን የግሉኮስ መጠን ይቀንሳል። የግሉካጎን መጠን መቀነስ ደግሞ በጉበት ውስጥ በግላይኮጅን መልክ ተከማችቶ የሚቀመጠውን ግሉኮስ ወደደም ዝውውር እንዳይገባ ያደርገዋል።
ምግብ ከተበላ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጂኤልፒ 1 እና ሌሎች ኢንክሪቲኖች በዲፒፒ 4 ኢንዛይም ይሰባበራሉ። በዲፒፒ 4 የተሰባበሩ ኢንክሪቲኖች (ጂኤልፒ-1 ን ጨምሮ) የደም ግሉኮስን ማስተካከል አይችሉም።
ኤክሰናታይድ የሚሰራው በተፈጥሮ ከሚገኘው ጂኤልፒ 1 ጋር በተመሳሳይ መንገድ ነው። ነገር ግን በተፈጥሮ እንደሚገኘው ጂኤልፒ 1 በዲፒፒ 4 አይሰባበርም። ስለዚህ በሰውነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቆየት እና የደም ግሉኮስን ማስተካከል ይችላል።
በተጨማሪ ጂኤልፒ 1 የምግብ መንሸራሸርን ያዘገያል። ይህም የሆድ መሙላት ወይም የመጥገብ ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል። በዚህ ምክንያት በምግብ መልኩ ወደሰውነት የሚገባው የግሉኮስን መጠን ይቀንሳል።
የኤክሰናታይድ አወሳሰድ
የሚወሰደውን መጠን እና ጊዜ ሀኪም ይወስናል። የሀኪምዎን ትእዛዝ ይከተሉ።
ባይዱርዮን ብዙ ጊዜ በየሳምንቱ (በየ 7 ቀኑ) በቆዳ ስር ይወጋል።
- በቀን በማንኛውም ሰአት መድሀኒቱን መወጋት ይቻላል።
- ምግብ ተበልቶም ሆነ ሳይበላ መድሀኒቱን መወጋት ይቻላል።
ባየታ ብዙ ጊዜ በቀን አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ በቆዳ ስር ይወጋል።
- ምግብ ከሚበላበት ጊዜ ቀደም ብሎ ባለው የአንድ ሰአት ጊዜ ውስጥ መወሰድ አለበት። ከምግብ በኋላ መውሰድ ጥሩ አይደለም።
- በቀን ሁለት ጊዜ በሚወሰድበት ጊዜ ከቁርስና ከእራት በፊት ባለው የአንድ ሰአት ጊዜ ውስጥ መውሰድ ይቻላል። (ከምሳ እና ከእራት በፊት መውሰድ ይቻላል ነገር ግን በሁለቱ የምግብ ሰአቶች መካከል የስድስት ሰአት ልዩነት መኖር አለበት)
ኤክሰናታይድ የሚወጋበት ቦታ ሆድ ክንድ ወይም ታፋ ላይ ብቻ መሆን አለበት። መድሀኒቱ ጡንቻ ወይም ደምስር ላይ መወጋት የለበትም።
ይህ መድሀኒት ከሌላ የሚወጉ መድሀኒቶች ጋር መቀላቀል የለበትም።
የኢንሱሊን እና ኤክሰናታይድ አጠገብ ለአጠገብ መወጋት የለበትም።
(የኤክሰናታይድን አጠቃቀም በዝርዝር ለማየት ወደጽሁፉ መጨረሻ “የኤክሰናታይድ አጠቃቀም” የሚለውን ርእስ ይመልከቱ። ከዚህ ርእስ ስር ሶስት የተለያዩ የአጠቃቀም መማሪያዎች እንደሚገኙ ያስተውሉ። )
መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?
ለባይዱርዮን፦ መድሀኒቱን እንዳስታወሱ ይውሰዱ። ነገር ግን የሚቀጥለው የባይዱርዮን መውሰጃ ጊዜ 3 ቀን ከቀረው የተረሳውን ትተው በሚቀጥለው የባይዱርዮን መውሰጃ ቀን የተለመደውን መጠን ይውሰዱ። የረሱትን ጨምረው ለመውሰድ አይሞክሩ
ለባየታ፦ በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ጊዜ የተለመደውን መጠን ይውሰዱ። የረሱትን ጨምረው ለመውሰድ አይሞክሩ።
የኤክሰናታይድ የጎን ጉዳት (Side-effect)
ኤክሰናታይድ የሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች የሚከተሉት የጎን ጉዳቶች ሊያጋጥማቸው ይችላል
- ማቅለሽለሽ
- ማስታወክ
- ተቅማጥ
- የማዞር ስሜት
- የመረበሽ ስሜት (nervousness)
- የሆድ ድርቀት
- የምግብ አለመንሸራሸር
- የምግብ አለመፈጨት ችግር
- መድሀኒት የተወጋበት ቦታ ህመም
- የራስምታት
እነዚህ የጎን ጉዳቶች ብዙ ግዜ መድሀኒቱ ሲጀመር አከባቢ ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን መድሀኒቱ ከሰውነት ጋር ሲላመድ ይተዋሉ። ካልተወ ወይም ከአቅም በላይ ከሆነ ግን ለሀኪም ማማከር ተገቢ ነው።
ለዚህ መድሃኒት የሃኪም ክትትል ያስፈልገኛል?
የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሀኪም ክትትል ያስፈልጋቸዋል። ይህም የሚደረገው
- የታዘዘላቸው መድሀኒት የደም ግሉኮሳቸውን በመቆጣጠር ያመጣውን ውጤት ለማወቅ
- በመድሀኒቱ ምክንያት የሚመጣ የጎን ጉዳት ካለ ለማወቅ
- በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጣ ሌላ ህመም (ለምሳሌ የኩላሊት በሽታ) ካለ በጊዜ ለማወቅ እና የሚያስፈልገውን ህክምና ለማድረግ ነው።
ኤክሰናታይድን ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ምንድነው?
ይህ መድሀኒት የሚሰራው ሀኪም ባዘዘው መሰረት በየእለቱ ሲወሰድ ነው።
ከመድሀኒቱ በተጨማሪ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግና አመጋገብ ማስተካከል የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋፆ አለው።
ይህ መድሀኒት የደም ግሉኮስን ያስተካክላል እንጂ የስኳር በሽታን አይፈውስም። የስኳር በሽታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ህመም ነው። የህክምናው አላማ የደም ግሉኮስን በመቀነስ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ ኩላሊት እና አይን) ላይ የሚያደርሰውን በሽታ መከላከል ነው። የደም ግሉኮስ ሲቀንስ ይህን መድሀኒት መውሰድ ማቆም የደም ግሉኮስ ተመልሶ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ የደም ግሉኮስ ቢስተካከል ወይም ጤንነት ቢሰማ እንኳን ይህን መድሀኒት ያለሀኪም ትእዛዝ ማቋረጥ አይመከርም።
ኤክሰናታይድ የማይታዘዝላቸው ሰዎች (Contraindication and limitations)
- ከዚህ በፊት ይህን መድሀኒት ወስደው አደገኛ የሰውነት መቆጣት (አደገኛ አለርጂ) ያጋጠማቸው ሰዎች
- አይነት አንድ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች
- ከስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ ኪቶአሲዶሲስ (diabetic ketoacidosis) ያጋጠማቸው ሰዎች ናቸው።
በተጨማሪ ለባይዱርዮን ብቻ
- በቤተሰብ ወይም ራሳቸው የታይሮይድ እጢ (thyroid tumor) ያለባቸው ሰዎች
የመድሀኒቱ መስተጋብር (Drug Interaction)
- በአፍ የሚወሰዱ የወሊድ መቆጣጠሪያ አንድ ሰአት ቀደም ብሎ መውሰድ ይቻላል።
- የሚከተሉትን መድሀኒቶች ኤክሰናታይድ ከመወሰዱ በፊት አንድ ሰአት ቀድሞ መውሰድ ያስፈልጋል።
- ለኢንፌክሽን የሚወሰዱ መድሀኒቶች
- አሲታሚኖፍን (acetaminophen/Tylanol)
- ከምግብ ጋር የሚወሰዱ ሌሎች መድሀኒቶች ካሉ ኤክሰናታይድን በማይወጉበት የምግብ ሰአት መውሰድ ይቻላል።
- ዋርፋሪን (Warfrin/Coumadin) ለአንዳንድ የደም መጓጎል እንዲሁም የልብ ህመሞች የሚታዘዝ የደም ማቅጠኛ መድሀኒት ነው። ዋርፋሪንንና ኤክሰናታይድን በሚወስዱ ጥቂት ሰዎች ላይ የዋርፋሪን የደም ማቅጠን ሀይል ሊጨምር ይችላል። የዋርፋሪን መድሀኒት ሲታዘዝ በየጊዜው የሚደረገው የላቦራቶሪ ምርመራ (INR) እስከሚስተካከል ድረስ ጥብቅ የህክምና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲሁም ዋርፋሪን የሚወስድ ታካሚ የደም መፍሰስ ምልክቶችን ማወቅ እና ጥንቃቄ መውሰድ አለበት።
አልኮል፦ እንደብዙ መድሀኒቶች ሁሉ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ አልኮል መጠጥ መጠጣት አይመከርም።
እርጉዝ ሴቶች፦ ለእርጉዝ ሴቶች ከኤክሰናታይድ የተሻለ መድሀኒት ሊኖር ይችላል። በእርግዝና ግዜ የስኳር በሽታን መቆጣጠር ለእናትም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት ማርገዟን ስታውቅ መድሀኒቱን ላዘዘላት ሀኪም እንድታሳውቅ ይመከራል።
የሚያጠቡ ሴቶች፦ የሚያጠቡ ሴቶች ይህን መድሀኒት ሲወስዱ ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ ሀኪማቸውን ያማክሩ።
ምግቦች፦ይህን መድሀኒት ሲወስዱ ጣፋጭ የሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ ካርቦሀይድሬት (carbohydrate) ያላቸውን ምግቦች (ለምሳሌ ዳቦ፣ ፓስታ፣ ጣፋጭ ፍራፍሬዎች) ይቀንሱ። ለስኳር በሽታ ተስማሚ የሆነ የአመጋገብ መከተል ለመድሀኒቱ መስራት እና ለአጠቃላይ ጤንነት ጥሩ ነው።
ሌሎች ጥንቃቄዎች
ለባይዱርዮን ብቻ
መርፌ የተወጉበት ቦታ መቁሰል፦ ባይዱርዮንን የወሰዱ ጥቂት ሰዎች መርፌ የሚወጉበት አከባቢ ሊቆስልባቸው ይችላል። ቁስሉ እየባሰበት ከሄደ (ውሀ ከቋጠረ መግል ከያዘ ወይም የማይድን ከሆነ) ለሀኪም ማሳየት ተገቢ ነው።
የታይሮይድ እጢ፦ ባይዱርዮንን የወሰዱ ጥቂት ሰዎች የታይሮይድ እጢ (Thyroid C-cell tumor) አጋጥሟቸዋል። ይህ የጎን ጉዳት ያጋጠማቸው ሰዎች በቤተሰብ ወይም ራሳቸው የታይሮይድ እጢ የነበረባቸው ሰዎች ናቸው። የህመም ምልክቶቹን ማወቅ እና ምልክቶቹ የታዩ እንደሆን ለሀኪም ማሳወቅ ያስፈልጋል። የዚህ ህመም ምልክቶች፦
- አንገት አከባቢ ህመም
- አንገት አከባቢ ሲዳስሱ ጠጣር ነገር (እጢ) መኖር
- የድምጽ መለወጥ
- ምግብ/መጠጥ ሲውጡ ማመም ወይም ለመዋጥ መቸገር
- የትንፋሽ ማጠር ናቸው።
ለባይዱርዮንና ለባየታ (ለሁሉም ኤክሰናታይድ መድሀኒቶች)
የምግብ መንሸራሸር ችግር (gastroparesis)፦ አይነት ሁለት የስኳር በሽታ ከሚያመጣው ህመም አንዱ የምግብ መንሸራሸር ችግር (gastroparesis) አንዱ ነው። ይህ ህመም ያለባቸው ሰዎች ኤክሰናታይድ (ባይዱርዮንን ወይም ባየታን) ከመውሰዳቸው በፊት ከሀኪማቸው ጋር ስለተሻለ አማራጭ ቢማከሩ ጥሩ ነው።
የጣፊያ ህመም (pancreatitis)፦ ኤክሰናታይድ የጣፊያ ህመም (pancreatitis) ሊያባብስ ይችላል። ይህ የጎን ጉዳት በተለይ የሀሞት ጠጠር ያለባቸውና የአልኮል መጠጥ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ላይ ሊታይ ይችላል። የዚህ ህመም ምልክቶች ሀይለኛ የማያቋርጥ እስከጀርባ ድረስ የሚሰማ የሆድ ህመም ማቅለሽለሽ ማስታወክ እና ዘይት ያለበት የሚመስል ሰገራ ሊሆን ይችላል። ይህን መድሀኒት እየወሰዱ እንዲህ ያለ ህመም የሚሰማው ሰው ለሀኪሙ እንዲያሳውቅ ይመከራል።
የኩላሊት በሽታ፦ በጥቂት ሰዎች ላይ ኤክሰናታይድ የኩላሊት በሽታን ሊያባብስ ይችላል። ከኤክሰናታይድ የጎን ጉዳቶች መካከል ማስታወክ እና ተቅማጥ ይገኙበታል። እነዚህ የህመም ምልክቶች የሰውነት ውሃ ይዘት መቀነስ (dehydration) ሊያስከትሉ ይችላሉ። የሰውነት ውሃ ይዘት መቀነስ የኩላሊት በሽታን ሊያባብስ ስለሚችል የኩላሊት ህመም ያለበት ሰው እንዲህ ያሉ ህመም ምልክቶች ከታዩበት ለሀኪም እንዲያሳውቅ ይመከራል። በተጨማሪ እንደአምራቹ መመሪያ መሰረት ኤክሰናታይድ የኩላሊት በሽታቸው ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ሰዎች ላይ መጀመር እንደሌለበት ይገልጻል። ይህን ለማወቅ ይህ መድሀኒት ከመታዘዙ በፊት ሀኪም ክርያቲኒን ክሊራንስ (Creatinine clearance) የሚባል የላቦራቶሪ ምርመራ ሊያዝ ይችላል። የዚህ ምርመራ ውጤት ከ30 ሚሊሊትር በደቂቃ (30 mL/min) ከሆነ ኤክሰንታይድ ለታካሚው አይሰጥም። የኩላሊት ጤንነትን ለማረጋገጥ በየጊዜው ይህ ምርመራ ሊታዘዝ ይችላል።
የሰውነት መቆጣት (አደገኛ አለርጂ)፦ አንዳንድ ሰዎች ለዚህ መድሀኒት አደገኛ የሰውነት መቆጣት (አደገኛ አለርጂ) ሊኖራቸው ይችላል። አናፍላክሲስና (Anaphylaxis) አንጂዮኢዴማ (Angioedema) አጣዳፊ ህክምና የሚያስፈልጋቸው አለርጂ አይነቶች ናቸው። የህመም ምልክቶች ከታዩ ሀኪም ጋር መሄድ አስፈላጊ ነው። ዋና ዋና ምልክቶች እነዚህን ያካትታል
- ለመተንፈስ መቸገር
- የፊት የምላስ የከንፈር ወይም የጉሮሮ ማበጥ
- የቆዳ ሽፍታ እና ማሳከክ
- የማዞር ስሜት
- የልብ ትርታ መጨመር
የደም ግሉኮስ ማነስ፦ ኤክሰናታይድ ብቻውን ሲወሰድ ዝቅተኛ የደም ግሉኮስ (hypoglycemia) አያመጣም። ነገር ግን ከሌሎች የስኳር በሽታ መድሀኒቶች ጋር እንደተጨማሪ በሚወሰድበት ጊዜ የዝቅተኛ የደም ግሉኮስ (Hypoglycemia) ምልክቶችንና መወሰድ ያለበትን ጥንቃቄ ማወቅ ያስፈልጋል።
ሀይፓግላይስሚያ (Hypoglycemia)
የደም ግሉኮስ ሲለካ ከ70 በታች ሲሆን ወይም አንዳንድ የህመም ምልክቶች ሲታዩ የደም ግሉኮስ ማነስ (Hypoglycemia) ይባላል። እንደከፍተኛ የደም ግሉኮስ ሁሉ ይህ የደም ግሉኮስ በጣም ዝቅ ማለት ለጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል።
ይህን የጎን ጉዳት ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮች ውስጥ መድሀኒቱን ያለምግብ መውሰድ፣ በቂ ምግብ አለመመገብ፣ እና ሌሎች አንዳንድ መድሀኒቶች ናቸው። እንዲሁም ከ65 አመት በላይ እድሜ ያላቸው ሰዎች ለዚህ ጎን ጉዳት የበለጠ የተጋለጡ ናቸው። ምልክቶቹን ማወቅ እና ጥንቃቄ ማድረግ ጥሩ ነው።
ዋና ዋና የህመም ምልክቶች
- የረሀብ ስሜት
- የመንቀጥቀጥ ስሜት
- በላብ መጠመቅ
- ብዥታ
- የሰውነት መዛል
- ያለተለመደ ግራ መጋባት (confusion)
- ራስ ማዞር
- የልብ በሀይል መምታት፣
- እንዲሁም ከባሰ እራስን መሳት ናቸው።
እነዚህ ምልክቶች የተሰማው ሰው ማድረግ ያለበት የሚከተሉትን ነው፦
- ከተቻለ የደም ግሉኮስ መለካት
- ይህ ካልተቻለ ወይም ተለክቶ የደም ግልኮስ ከ70 በታች ከሆነ ስኳርነት ያለው ምግብ ወይም መጠጥ መውሰድ። ለምሳሌ የግሉኮስ ታብሌት፣ አንድ ማንኪያ ስኳር፣ ማር፣ ከረሜላ፣ ግማሽ ብርጭቆ የብርቱካን ጭማቂ ወይም አንድ ብርጭቆ ወተት መውሰድ ይቻላል።
- ከ15 ደቂቃ በሁዋላ የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ በድጋሚ መለካት።
- ተለክተው ከ70 በላይ ከሆነ ቀለል ያለ ምግብ መመገብ
- ተለክተው ከ70 በታች ከሆነ ከ 1 –3 ያሉትን የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ እስኪሆን ድረስ መደጋገም።
- የስኳር በሽታዎን ለሚከታተል ሀኪምዎ መንገር አይርሱ።
ለባይዱርዮን ጥብቅ ማስጠንቀቂያ (FDA Blackbox Warning)
- በቤተሰብ ወይም የታይሮይድ ካንሰር ወይም እጢ (thyroid tumor) ያለባቸው ወይም የነበረባቸው ሰዎች ይህ መድሀኒት መውሰድ የለባቸውም።
- በቤተሰብ ወይም ራሳቸው የኢንዶክሪን ኒዮፕላዝያ ሲንድሮም (Multiple Endocrine Neoplasia Syndrome) ያለባቸው ሰዎች ይህ መድሀኒት መውሰድ የለባቸውም።
መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ
- ያልተጀመረ መድሀኒት ማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) ውስጥ ይቀመጣል። በረዶ በሚሰራበት ቦታ (freezer) ውስጥ መቀመጥ የለበትም። መድሀኒቱ በረዶ ከሰራ ይበላሻል። ስለዚህ ማቀዝቀዣው ውስጥ በረዶ ከሚሰራው ክፍል ርቆ መቀመጥ አለበት።
- ይህ መድሀኒት እርጥበት በሌለበት ህጻናት በማይደርሱበት ቦታ መቀመጥ አለበት።
- የኤክሰናታይድ ከማቀዝቀዣ ከወጣ ከ 30 ኛው ቀን በኋላ ከአገልግሎት ውጭ ይሆናል።
1. የባይዱሩዮን መርፌ አጠቃቀም (Bydureon Single-Dose Tray)
አንድ የባይዱርዮን ካርቶን አራት የመድሀኒት ማዘጋጃ ትሪዎችን ይይዛል። አንድ ትሪ ውስጥ የሚከተሉት ይገኛአሉ
- አንድ ባይዱርዮን የሚይዝ የመድሀኒት ብልቃጥ
- አንድ ሲሪንጅ
- ሁለት መርፌዎች
- አንድ የመድሀኒት ብልቃጥ ማያያዣ
መድሀኒቱን ለመወጋት የሚያስፈልጉ ሌሎች ነገሮች
- የአልኮል ስዋብ (ወይም አልኮል እና ጥጥ)
- መርፌ ለመጣያ የሚሆን እቃ (የሚከደንና መርፌ የማይወጋው ጠንካራ እቃ)
- ንጹህ ጠረጴዛ
ይህ መመሪያ አራት ክፍሎች አሉት። እያንዳንዱን ክፍል ማንበብ እስፈላጊ ነው።
ሀ
የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማዘጋጀት
- አንድ የመድሀኒት ትሪ ከማቀዝቀዣ (ከፍሪጅ) ማውጣት
- መድሀኒቱን ከትሪው ውስጥ ከማውጣት በፊት እጅን በውሀ እና በሳሙና መታጠብ
- የትሪውን የወረቀት ሽፋን መላጥ። ሲሪንጁን አውጥቶ ውስጡ የሚገኘውን ፈሳሽ መመርመር
- ሲሪንጁ ውስጥ ያለው ፈሳሽ እንደውሀ ቀለም የሌለው እና ምንም አይነት ጠጣር (ጓጓላ ነገር) እንደሌለው ማየት ውስጡ ትንንሽ አየር የያዙ እንክብሎች ቢኖሩ ምንም ችግር የለውም።
- መርፊውን ማውጣትና ሰማያዊ ክዳኑን ጠምዝዞ ክዳኑን ማላላት። ይህንን በኋላ ስለሚያስፈልግ ቅርብ ማስቀመጥ።
- የመድሀኒቱን ብልቃጥ ውስጥ ነጭ ዱቄት የመሰለ ነገር አለ። ዱቄቱ የተጋገረ ወይም የተያያዘ ነገር ካለው መፍታታት አለበት። ስለዚህ ብልቃጡን ዘቅዝቀው ከጠረቤዛ ጋር በማማታት ዱቄቱን ማፍታታት ይቻላል።
- የመድሀኒቱን ብልቃጥ አረንጋዴ ክዳን ማንሳት። ክዳኑን መጣል ይቻላል። ብልቃጡን ቅርብ ማስቀመጥ።
ለ
የመድሀኒቱን ብልቃጥ ከሲሪንጅ ጋር ማያያዝ
- የብልቃጡን ማያያዣ መክፈት። ውስጡ ብርቱካናማ ማያያዣ ይገኛል። ይህንን ብርቱካናማ ማያያዣ በእጅ መነካት የለበትም።
- በአንድ እጅ የብልቃጡን ማያያዣ ሽፋን እንደተያዘ በሌላ እጅ የመድሀኒቱን ብልቃጥ በመያዝ ብልቃጡን እና ማያያዣውን በሀይል ማጣበቅ
- ሲሪንጁን ከዚህ በታች እንደሚታየው መያዝ። በሌላ እጅ የሲሪንጁ ነጭ ክዳን ላይ የሚገኙ ሁለት ጥቁር ምልክቶችን በመያዝ ነጩን ክዳን መስበር። በዚህ ግዜ የመድሀኒቱ መወርወሪያ ወደውስጥ እንዳይገባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። የተሰበረውን ነጭ ክዳን መጣል ይቻላል።
- የመድሀኒቱን ብልቃጥ በአንድ እጅ ሲሪንጁን በሌላ እጅ በመያዝ እያዞሩ ማጣበቅ። አሁንም የመድሀኒቱ ብልቃጥ ላይ የተያያዘውን ብርቱካናማ ማገናኛ በእጅ መንካት አያስፈልግም። ሲሪንጁና ብልቃጡ ሲያያዝ በሀይል መጥበቅና በሀይል መላላት የለበትም። በትክክል ግጥም ማለት አለበት።
ሐ
መድሀኒቱን ማደባለቅ እና ሲሪንጅ ውስጥ መገልበጥ
አንዴ መድሀኒቱ እና ፈሳሹ ከተደባለቀ በኋላ መድሀኒቱን ወድያው መወጋት ያስፈልጋል። ከተደባለቀ በኋላ ማቆየት መድሀኒቱን ያበላሸዋል።
- ከታች እንደሚታየው የሲሪንጁን መወርወርያ ወደታች በመጫን ሲሪንጁ ውስጥ ያለውን ፈሳሽ ወደመድሀኒቱ ብልቃጥ መገልበጥ። በዚህ ግዜ የመድሀኒቱ መወርወርያ ለመግፋት ያስቸግር ይሆናል። ይህ ትክክል ነው። መወርወሪያው ወደላይ ለመውጣት ቢፈልግም አጥብቆ ከታች እንደሚታየው በአውራ ጣት አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል።
- የሲሪንጁን መወርወርያ ወደታች እንደተያዘ የተጣበቀውን ብልቃጥ እና ሲሪንጅ በሀይል ላይ ታች መነቅነቅ። ዱቄቱና ፈሳሹ በደንብ እስከሚዋሀድ ድረስ መበጥበጥ። ይህ ሲደረግ ብልቃጡ ይወድቃል ብሎ መፍራት አያስፈልግም። ማያያዣው አጥብቆ ይይዘዋል።
- የመድሀኒቱ ዱቄት እና ፈሳሹ በደንብ ሲደባለቅ ነጭ ወይም እንደዳመና ያለ ቀለም ይኖረዋል። ብልቃጡን እያዟዟሩ የጓጎለ ወይም ጠርሙሱ ላይ የተጣበቀ ዱቄት አለመኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የዱቄት ምልክት ካለ እስኪጠፋ ድረስ መበጥበጥ ያስፈልጋል።
- ዱቄቱ እና ፈሳሹ ከተዋሀደ በኋላ ብልቃጡን ወደላይ አድርጎ መዘቅዘቅ እና ብልቃጡን በጣት መታ መታ ማድረግ። ይህ ሲደረግ የሲሪንጁን መወርወሪያ አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል።
- የሲሪንጁን መወርወርያ ወደታች በመሳብ ፈሳሹን ወደሲሪንጁ መገልበጥ። የመወርወሪያው ጥቁር መድፈኛ ስሪንጁ ላይ የሚታይ ጥቁር ነጠብጣብ እስከሚያልፍ ድረስ መሳብ። ሲሪንጁ ውስጥ አየር ወይም አረፋ ቢኖር ችግር የለውም። ትንሽ ፈሳሽ ከብልቃጡ ውስጥ ሊቀር ይችላል።
- መወርወርያው እንዳይንቀሳቀስ ከታች እንደሚታየው የሲሪንጁን መወርወርያ በአንድ እጅ መያዝ። በሌላ እጅ ብርቱካናማውን ማያያዣ በመጠምዘዝ ማውለቅ።
መ
መድሀኒቱን መወጋት
- አብሮ የሚመጣውን መርፌ ከሲሪንጁ ጋር ማያያዝ እና በማዞር ማጥበቅ። የመርፌውን ክዳን አይነሳ።
- ትክክለኛውን የመድሀኒት መጠን ለማግኘት ይህንን በጥንቃቄ ማድረግ አለብዎ፤ በቀስታ የሲሪንጁን መወርወርያ በመግፋት ከጥቁሩ ነጠብጣብ ጋር ማስተካከል። አንዴ ከተስተካከለ በኋላ መወርወሪያው እንዳይንቀሳቀስ መጠንቀቅ። ንጹህ ቦታ ላይ ሲሪንጁን ማስቀመጥ።
- መድሀኒቱን የሚወጋበትን ቦታ መምረጥ። ታፋ ሆድ ወይም ክንድ ላይ መወጋት ይቻላል። በየሳምንቱ ሆድ ላይ (ወይም የመረጡት ቦታ ላይ) መወጋት ይቻላል። ግን የሚወጋበት ቦታ ማፈራረቅ ጥሩ ነው (ለምሳሌ በዚህ ሳምንት ከእንብርት ግራ በኩል ከተወጋ በሚቀጥለው ሳምንት ከእንብርት ቀኝ በኩል መወጋት ይቻላል።)
- የሚወጋበትን ቦታ በአልኮል ስዋብ (ወይም በውሀና በሳሙና) ማጽዳት
- ሲሪንጁን ጥቁሩ ነጠብጣብ ላይ መያዝ። በሌላ እጅ የመርፌውን ክዳን መንቀል። ይህ ሲደረግ የመርፌው ጫፍ ላይ ፈሳሽ ሊኖር ይችላል። ይህ ችግር የለውም።
- የመርፌውን ጫፍ ወደመወጊያ ቦታ ይክተቱት
- የሲሪንጁን መወርወርያ መሄድ እስከሚችለው ድረስ መግፋትና መርፌውን መንቀል.። በዚህ ጊዜ የሲሪንጁ መወርወሪያ አልንቀሳቀስ ካለ መርፌው ተደፍኖ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መርፊውን ከሰውነት መንቀልና በሁለተኛው (ትርፍ ሆኖ በምመጣው) መርፌ መተካት ይቻላል።
- መርፊውን ጠንካራ ክዳን ያለው እቃ ውስጥ ከሌላ ቁሻሻ ለይቶ ማስወገድ።
2. የባይዱርዮን ፔን አጠቃቀም (Bydureon Pen)
የሚያስፈልጉ ነገሮች
- አንድ የባይዱርዮን ፔን ትሪ (በውስጡ ለአንድ ግዜ የሚሆን የባይዱርዮን ፔን እና አንድ የፔን መርፌ ይኖረዋል)
- አልኮል ስዋብ
- መርፌ ለመጣያ የሚሆን እቃ (የሚከደንና መርፌ የማይወጋው ጠንካራ እቃ)
ሀ
የባይዱርየን ፔንን ማዘጋጀት
- የባይዱርየንን ፔን ከፍሪጅ ማውጣት
- ቅዝቃዜው እስንዲለቀው ለ15 ደቂቃ መቆየት
- እጅን በውሀ እና በሳሙና መታጠብ
- የመድሀኒቱን የወረቀት ሽፋን ልጦ ማንሳት
- የመድሀኒቱን ፔን እና መርፌ ማውጣት
- መድሀንቱን በማሳያ መስኮት በኩል የሚታየው ፈሳሽ ንጹህ እንደውሀ ቀለም የሌለውና ጠጣር (ጓጓላ) ነገር እንደሌለው ማረጋገጥ። ፈሳሹ ቀለም ወይም የጓጎለ ነገር ካለው ይህንን ፔን መጠቀም አያስፈልግም።
- ውስጡ አየር የቋጠረ እንክብል ቢታይ ችግር የለውም
- ከመርፌው ላይ የወረቀት ሽፋኑን ልጦ ማንሳት
- መርፊውን ከፔኑ ጋር ማያያዝና እያዞሩ ማሰር። የመርፌውን ክዳን አሁን ማንሳት አያስፈልግም።
- ፔኑን ወደላይ (መርፊው ወደላይ ሆኖ) ቀጥ ተደርጎ እንደተያዘ የመጠምዘዣ እጄታውን ቀስ ብሎ ማዞር። “ቀጭ” ወይም “ክሊክ” የሚል ድምፅ ሲሰማ እንዲሁም አረንጋዴው ሽፋን ሲጠፋ በትክክል ዞሯል ማለት ነው።
ለ
መድሀኒቱን ማደባለቅ
ፔኑን ብርቱካናማ ሽፋኑ ላይ ይያዝና ወደሌላው እጅ መዳፍ ላይ ማማታት። ይህንን ቢያንስ ሰማንያ (80) ጊዜ መድገም።
- ይህ ሲደረግ መጠምዘዣ እጀታው እንዳይዞር መጠንቀቅ ያስፈልጋል
- በአስር ጊዜ አንዴ ፔኑን ማዞር ያስፈልጋል (ማለትም አስር ጊዜ ከተመታ በኋላ ፔኑን ማዞር ከዛ እንደገና አስር ጊዜ መምታት እያሉ መቀጠል ማለት ነው)
በቂ ብርሀን ወዳለበት ቦታ ሄዶ ሲደባለቅ የሚያሳይ መስኮት ውስጥ የተደባለቀውን ፈሳሽ መመልከት
- ሁለት ሲደባለቅ የሚያሳይ መስኮት አለ። ሁለቱንም መመልከት ያስፈልጋል።
- በደንብ ሲደባለቅ ነጭ (ደመና የሚመስል) ፈሳሽ ይታያል። ምንም አይነት የጓጎለ ነገር አይታይም። ከዚህ በታች ያለውን ምስል ይመልከቱ
- በደንብ ካልተደባለቀ ፔኑ በቂ የመድሀኒት መጠን አይሰጥም። ስለዚህ አስከሚደባለቅ ድረስ መምታት ያስፈልጋል።
- መድሀኒቱ ከተደባለቀ በኋላ ወዲያው መወጋት ያስፈልጋል። ከቆየ መድሀኒቱ ይበላሻል።
ሐ
መድሀኒቱን መወጋት
- መድሀኒቱን የሚወጋበትን ቦታ መምረጥ። ታፋ ሆድ ወይም ክንድ ላይ መወጋት ይቻላል። በየሳምንቱ ሆድ ላይ (ወይም የመረጡት ቦታ ላይ) መወጋት ይቻላል። ግን የሚወጋበት ቦታ ማፈራረቅ ጥሩ ነው (ለምሳሌ በዚህ ሳምንት ከእንብርት ግራ በኩል ከተወጋ በሚቀጥለው ሳምንት ከእንብርት ቀኝ በኩል መወጋት ይቻላል።)
- የሚወጋበትን ቦታ በአልኮል ስዋብ ማጽዳት.።
- ፔኑን ወደላይ (መርፊው ወደላይ እንደሆነ) አድርጎ መያዝና የመጠምዘዣ እጄታውን ማዞር
- ብርቱካናማው ሽፋን ሲጠፋ በትክክል ዞሮ ጨርሷል ማለት ነው።
- ይህ ሲደረግ ነጭ የመጫኛ ቁልፍ ይወጣል። ይህንን አንዳይጫኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
- የመርፌውን ክዳን ጎትቶ ማንሳት (ማዞር አያስፈልግም)
- ይህ ሲደረግ ትንሽ ፈሳሽ የመርፊው ጫፍ ላይ ሊታይ ይችላል። ይህ ችግር የለውም።
- በአልኮል ስዋብ የተጸዳው ሰውነት ላይ መርፌውን መውጋት።
- “ቀጭ” ወይም “ክሊክ” የሚል ድምጽ እስከሚሰማ ድረስ የመጫኛ ቁልፉን መጫን። ከዛም ለ10 ሰከንድ (ቀስ እያሉ እስከአስር መቁጠር)
- መርፊውን መንቀልና መርፌ መጣያ እቃ ውስጥ መጨመር።
3. የባየታ ፔን (Byetta Pen) አጠቃቀም
የባየታ ፔን ሁለት የመድሀኒት መጠን በሚሰጥ ፔን መልኩ ይዘጋጃል። አንደኛው 5 ማይክሮግራም (5 mcg) መድሀኒት ይሰጣል ሁለተኛው 10 ማይክሮግራም (10 mcg) መድሀኒት ይሰጣል። የሁለቱ ፔኖች አጠቃቀም አንድ አይነት ነው።
ሀ
የባየታ ፔንን ማዘጋጀት ወይም አክቲቬት ማድረግ
አዲስ የባየታ ፔን ከመጀመሩ በፊት መዘጋጀት ወይም አክቲቬት መደረግ አለበት። ይህ የሚደረገው ለአንድ ፔን አንድ ጊዜ ብቻ ነው። የባየታን ፔን የሚዘጋጀው ወይም አክቲቬት የሚደረገው እንደሚከተለው ነው፦
- እጅ በውሀ እና በሳሙና መታጠብ
- የፔኑን ክዳን ማንሳት እና ውስጡ ያለው መድሀኒት ንጹህ እንደውሀ ቀለምና ጠጣር (ጓጓላ) ነገር እንደሌለው ማረጋገጥ። ትንንሽ የአየር እንክብሎች ቢኖሩ ችግር የለውም። ቀለሙ ከተለወጠ ወይም ውስጡ ጠጣር የሚመስል ነገር ካለው ይህንን ፔን መጠቀም አያስፈልግም።
- መርፌውን ከፔኑ ጋር ለማያያዝ መርፌው ጀርባ ያለውን መሸፈኛ ወረቀት መላጥ። ከዛም መርፌውን ከፔኑ ጋር አገናኝቶ እያዞሩ ማጥበቅ።
- የመርፌውን የውጭ ክዳን ጎትቶ ማንሳት። ይህንን ክዳን በኋላ ስለሚያስፈልግ ቅርብ ማስቀመጥ።
- የመርፌውን የውስጥ ክዳን ጎትቶ ማንሳት። ይህንን የውስጥ ክዳን መጣል ይቻላል። የመርፌው ጫፍ ላይ ፈሳሽ ነገር ሊታይ ይችላል። ይህ ችግር የለውም።
- የፔኑን ምልክት ማሳያ ላይ ወደቀኝ የሚጠቁም ቀስት እንዳለ ማረጋገጥ። ይህ ምልክት ከሌለ የመሙያ እጄታውን እስከሚሄድ ድረስ ማዞር ያስፈልጋል። የመሙያ እጄታው ዞሮ ሲያበቃ የማሳያ መስኮቱ ላይ ወደ ቀኝ የሚጠቁም ቀስት ይታያል።
- የመሙያ እጄታውን እስከሚሄደው ድረስ መሳብ። በትክክል የተሳበ እንደሆነ የማሳያ መስኮቱ ላይ ወደላይ የሚጠቁም ቀስት ይኖራል።
- የመሙያ እጄታውን ከሰውነት ተቃራኒ አቅጣጫ ማዞር። በትክክል ሲዞር የማሳያ መስኮቱ ላይ የሚወሰደው የመድሀኒት መጠን ይታያል (ለምሳሌ 5 ማይክሮግራም የሚወሰድ ከሆነ ማሳያ መስኮቱ ላይ “5” ቁጥር ይታያል)
- መርፊው ከሰውነት ተቃራኒ አቅጣጫ እንደጠቆመ ፔኑን ወደላይ አድርጎ መያዝ። መድሀኒቱን ለማፍሰስ የመጫኛ ቁልፉን ለአምስት ሰከንድ ተጭኖ መቆየት። መድሀኒቱ ሲፈስ ካልታየ ከቁጥር 7 አንስቶ እስከ 10 ድረስ ያለውን መደጋገም።
- ደጋግሞ መድሀኒቱን ለማፍሰስ ሞክሮ ካልተሳካ መርፊውን ቀይሮ መሞከር ይቻላል።
- መድሀኒቱ ሲፈስ ከታየ በኋላ እና የማሳያ መስኮቱ ላይ ወደላይ የሚጠቁም ቀስት ሲታይ ፔኑ ተዘጋጅቷል ማለት ነው።
- የመሙያ እጄታውን ከሰውነት ወደተቃራኒ አቅጣጫ ማዞር። የማሳያ መስኮቱ (3) ላይ ወደቀኝ የሚጠቁም ቀስት ይታያል። አሁን ፔኑ ተዘጋጅቷል። ይህንን ፔን ድጋሚ ማዘጋጀት አያስፈልግም።
- ከዚህ በኋላ መድሀኒቱን ለመወጋት ወደሚቀጥለው ክፍል ይመልከቱ። መድሀኒቱን ለመውሰድ ዝግጁ ካልሆኑ መርፊውን መንቀልና ፔኑን በራሱ ክዳን መክደን አይዘንጉ።
- መርፌውን ለመንቀል መጀመሪያ በመርፌው የውጭ ክዳን መሸፈን። መርፊውን እያዞሩ ማውለቅ እና ተገቢ በሆነ የመርፌ መጣያ እቃ ውስጥ መጣል።
ለ
የእለት ተእለት አጠቃቀም
- እጅን በውሀ እና በሳሙና መታጠብ
- የፔኑን ክዳን ማንሳት እና ውስጡ ያለው መድሀኒት ንጹህ መሆኑን ማረጋገጥ። ይህ መድሀኒት እንደውሀ ቀለምና ጓጓላ ነገር የሌለው መሆን አለበት። ትንንሽ የአየር እንክብሎች ብኖሩ ችግር የለውም። ቀለሙ ከተለወጠ ወይም ውስጡ ጠጣር የሚመስል ነገር ካለው ይህንን ፔን መጠቀም አያስፈልግም።
- መርፊ ከፔን ጋር ለማያያዝ መርፌው ጀርባ ያለውን መሸፈኛ ወረቀት መላጥ። ከዛም መርፌውን ከፔኑ ጋር አገናኝቶ እያዞሩ ማጥበቅ።
- የመርፌውን የውጭ ክዳን ጎትቶ ማንሳት። ይህንን ክዳን በኋላ ስለሚያስፈልግ ቅርብ ማስቀመጥ።
- የመርፌውን የውስጥ ክዳን ጎትቶ ማንሳት። ይህንን የውስጥ ክዳን መጣል ይቻላል። የመርፌው ጫፍ ላይ ፈሳሽ ነገር ሊታይ ይችላል። ይህ ችግር የለውም።
- የፔኑን ምልክት ማሳያ ላይ ወደቀኝ የሚጠቁም ቀስት እንዳለ ማረጋገጥ። ይህ ምልክት ከሌለ የመሙያ እጄታውን እስከሚሄድ ድረስ ማዞር ያስፈልጋል። የመሙያ እጄታው ዞሮ ሲያበቃ የማሳያ መስኮቱ ላይ ወደ ቀኝ የሚጠቁም ቀስት ይታያል።
- የመሙያ እጄታውን እስከሚሄደው ድረስ መሳብ። በትክክል የተሳበ እንደሆነ የማሳያ መስኮቱ ላይ ወደላይ የሚጠቁም ቀስት ይኖራል።
- የመሙያ እጄታውን ከሰውነት ተቃራኒ አቅጣጫ ማዞር። በትክክል ሲዞር የማሳያ መስኮቱ ላይ የሚወሰደው የመድሀኒት መጠን ይታያል (ለምሳሌ 5 ማይክሮግራም የሚወሰድ ከሆነ ማሳያ መስኮቱ ላይ “5” ቁጥር ይታያል)
- መድሀኒቱን የሚወጋበትን ቦታ መምረጥ። ታፋ ሆድ ወይም ክንድ ላይ መወጋት ይቻላል። የሚወጋበት ቦታ ማፈራረቅ ጥሩ ነው።
- የሚወጋበትን ቦታ በአልኮል ስዋብ ማጽዳት.።
- መርፊውን መውጋትና የመጫኛ ቁልፉን ተጭኖ ቀስ እያሉ እስከአምስት መቁጠር ወይም አምስት ሰከንድ መቆየት። መርፊውን ቶሎ መንቀል ወይም የመጫኛ ቁልፉን ሳይጫኑ መቆየት በቂ መድሀኒት እንዳያገኙ ያደርጋል። ስለዚህ መርፊውን ከተወጉና መጫኛ ቁልፉን ከተጫኑ በኋላ ለአምስት ሰከንድ መቆየት አስፈላጊ ነው።
- አንዳንድ ጊዜ ከተወጋ በኋላ መርፊው ጫፍ ላይ ትንሽ ፈሳሽ ሊኖር ይችላል። ከአንድ ጠብታ በላይ ፈሳሽ መርፌው ጫፍ ላይ ካለ የተወጋው በቂ መድሀኒት ላይሆን ይችላል። ይህንን ለማካካስ ድጋሚ መወጋት ትክክል አይደለም። ነገር ግን ይህ እንዳይሆን መርፊው ከተወጋ በኋላ ከሰውነት ጋር መርፌውን ጠበቅ አድርጎ መያዝ እንዲሁም መጫኛ ቁልፉን ተጭኖ በቂ ጊዜ መቆየት ጥሩ ነው።
- መርፊውን መንቀል እና ማሳያ መስኮቱ (3) ላይ ወደላይ የሚጠቁም ቀስት መኖሩን ማረጋገጥ።
- የመሙያ እጄታውን ከሰውነት ተቃራኒ ወደሆነ አቅጣጫ መጠምዘዝ። የማሳያ መኮቱ ላይ ወደቀኝ የሚጠቁም ቀስት ይታያል።
- መርፌውን በመርፊው የውጭ ክዳን መሸፈን። መርፊውን እያዞሩ ማውለቅ እና ተገቢ በሆነ የመርፌ መጣያ እቃ ውስጥ መጣል።
- ፔኑን በክዳኑ መክደንና ርጥበትና ሙቀት የሌለበት ህጻናት የማይደርሱበት ቦታ ማስቀመጥ።
ማጣቀሻ
- Brunton, Laurence L., et al. Goodman & Gilman’s: the Pharmacological Basis of Therapeutics. McGraw Hill Medical, 2018.
- BYDUREON® (exenatide extended-release). [package insert]. Wilmington, DE 19850: AstraZeneca Pharmaceuticals LP.; 2020.
- BYETTA® (exenatide) Injection. [package insert]. Wilmington, DE 19850: AstraZeneca Pharmaceuticals LP 2018.
- BYETTA® (exenatide) Injection. [package insert]. San Diego, CA 92121: Amylin Pharmaceuticals, Inc.; 2009.
- dailymed.nlm.nih.gov/dailymed/lookup.cfm?setid=5a9ef4ea-c76a-4d34-a604-27c5b505f5a4#i4i_dosage_admin_id_7b31fa3a-1f64-4c9e-8c27-4f4f6133f24e.
- “Diabetes Mellitus.” Pharmacotherapy Handbook, by Barbara G. Wells et al., McGraw-Hill Education, 2017, pp. 161–175.
- “Exenatide.” Drugs and Lactation Database (LactMed) [Internet]., U.S. National Library of Medicine, 1 May 2019, www.ncbi.nlm.nih.gov/books/NBK500978.
ቀን: 02/16/21
Disclaimer: All pictures and diagrams used in this post are not HIA’a property.
የኤክሰናታይድ ኩፓኖች
ኤክሰናታይድ ከሌሎች የስኳር በሽታ መድሀኒቶች ጋር ሲወዳደር ዋጋው በጣም ውድ ነው።
የአምራቹ ኩፓን
የኤክሰናታይድ (የባይዱርዮንና ባየታ) አምራች ለተጠቃሚዎች ቅናሽ ይሰጣል። ነገር ግን ማመልከቻ ማስገባትና መስፈርቶችን ማሟላት ያስፈልጋል። ሁሉንም መስፈርት ለማየት የአምራቹን ድረገፅ ይጎብኙ።