አሎግልፕቲን ለምን ይታዘዛል?
አሎግልፕቲን በአይነት ሁለት ስኳር በሽታ ህመምተኞች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል ይረዳል።
አሎግልፕቲን በምን መልኩ ይመረታል?
አሎግልፕቲን በአፍ የሚዋጥ ኪኒን ነው። ብዙ ጊዜ በ25፣ 12.5 ፣ እና 6.25 ሚሊግራም መጠን ይመጣል።
አሎግልፕቲን እንዴት ነው የሚሰራው?
አንድ ሰው ምግብ ሲበላ ወይም የደም ግሉኮሱ ከፍ ሲል ኢንክሪቲን የሚባሉ ሆርሞኖች አንጀት አከባቢ ይመነጫሉ። ኢንክሪቲኖች በጣፊያ ውስጥ የኢንሱሊን ምርት እንዲጨምር እንዲሁም የግሉካጎን ምርት እንዲቀንስ ምልክት ይሰጡታል። የኢንሱሊን መጠን መጨመር በደም ያለውን የግሉኮስ መጠን ይቀንሳል። በአንጻሩ ከጣፊያ የሚመረተው እና የሚመነጨው የግሉካጎን መጠን መቀነስ በጉበት ውስጥ ተከማችቶ የሚቀመጠውን ግላይኮጅን ወደግሉኮስ ተለውጦ ወደደም ዝውውር እንዳይገባ ያደርገዋል። ስለዚህ የኢንሱሊንን ምርት በመቆጣጠር ኢንክሪቲኖች የደም ግሉኮስን ይቀንሳሉ። የደም ግሉኮስ የሚፈለገውን ያህል ዝቅ ካለ በኋላ ዲፒፒ 4 የሚባሉ ኢንዛይሞች ኢንክሪቲን በሚገኝበት የአንጀት አከባቢ ይመነጫሉ። ኢንክሪቲኖችን በመሰባበር ለጣፊያ የሚሰጡትን ምልክት እንዲያቆም ያደርጋሉ።
ይህ መድሀኒት ዲፒፒ 4 ኢንዛይሞች ኢንክሪቲኖችንን እንዳይሰባብሩ በማድረግ ኢንክሪቲኖች ለረጅም ግዜ በሰውነት እንዲቆዩ ያደርጋሉ። ኢንክሪቲኖች ለረጅም ግዜ በሰውነት መቆየት የኢንሱሊን ምርት እንዲቀጥልና የግሉካጎን ምርት እንደቀነሰ እንዲቆይ ያደርጋሉ። የዚህ አጠቃላይ ውጤት በደም ውስጥ የሚገኘው የግሉኮስ መጠን ማስተካከል ይሆናል።
የአሎግልፕቲን አወሳሰድ
- የሀኪም ትእዛዝ ይከተሉ።
- ብዙ ግዜ በቀን አንድ ግዜ ይወሰዳል።
- መድሀኒቱ የሚወሰድበት ሰአት ተመሳሳይ ቢሆን ይመረጣል።
- ከምግብ ጋር ወይም ያለምግብ ብቻውን መውሰድ ይቻላል።
መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?
ወድያው እንዳስታወሱ ይውሰዱ። ብዙ ሰአት ካለፈ ግን ይተውት እና በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ጊዜ የተለመደውን መጠን ይዋጡ። የረሱትን ጨምረው ለመዋጥ አይሞክሩ።
የመድሀኒቱ የጎን ጉዳት (Side-effect)
ይህን መድሀኒት የሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች ላይ እነዚህ የህመም ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ
- እንደጉንፋን (Nasopharyngitis) ያለ ህመም (ከአፍንጫ የሚወጣ ፈሳሽ (ንፍጥ)፣ የአፍንጫ መደፈን፣ የጉሮሮ ህመም)
- ራስምታት
ይህ ብዙ ግዜ መድሀኒቱ ሲጀመር አከባቢ የሚሰማ ህመም ነው። መድሀኒቱ ከሰውነት ጋር ሲላመድ ይተዋል። ካልተወ ወይም ከአቅም በላይ ከሆነ ግን ለሀኪም ያሳውቁ።
ለዚህ መድሃኒት የሃኪም ክትትል ያስፈልገኛል?
የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሀኪም ክትትል ያስፈልጋቸዋል። ይህም የሚደረገው
- የታዘዘላቸው መድሀኒት የደም ግሉኮሳቸውን በመቆጣጠር ያመጣውን ውጤት ለማወቅ
- በመድሀኒቱ ምክንያት የሚመጣ የጎን ጉዳት ካለ ለማወቅ
- በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጣ ሌላ ህመም (ለምሳሌ የኩላሊት በሽታ) ካለ በጊዜ ለማወቅ እና የሚያስፈልገውን ህክምና ለማድረግ ነው።
ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ምንድነው?
ይህ መድሀኒት የሚሰራው ሀኪም ባዘዘው መሰረት በየእለቱ ሲወሰድ ነው።
ከመድሀኒቱ በተጨማሪ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግና አመጋገብ ማስተካከል የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋፆ አለው።
ይህ መድሀኒት የደም ግሉኮስን ያስተካክላል እንጂ የስኳር በሽታን አይፈውስም። የስኳር በሽታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ህመም ነው። የህክምናው አላማ የደም ግሉኮስን በመቀነስ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ ኩላሊት እና አይን) ላይ የሚያደርሰውን በሽታ መከላከል ነው። የደም ግሉኮስ ሲቀንስ ይህን መድሀኒት መውሰድ ማቆም የደም ግሉኮስ ተመልሶ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ የደም ግሉኮስ ቢስተካከል ወይም ጤንነት ቢሰማ እንኳን ይህን መድሀኒት ያለሀኪም ትእዛዝ ማቋረጥ አይመከርም።
አሎግልፕቲን የማይታዘዝላቸው ሰዎች (Contraindication and limitations)
- ከዚህ በፊት ይህን መድሀኒት ወስደው አደገኛ አለርጂ ያጋጠማቸው ሰዎች
- አይነት አንድ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች እንዲሁም
- ከስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ ኪቶአሲዶሲስ (diabetic ketoacidosis) ያጋጠማቸው ሰዎች።
የመድሀኒቱ መስተጋብር (Drug Interaction)
አልኮል፦ እንደብዙ መድሀኒቶች ሁሉ አሎግልፕቲን ሲወስዱ አልኮል መጠጥ መጠጣት አይመከርም።
ምግቦች፦ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ ጣፋጭ የሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ ካርቦሀይድሬት (carbohydrate) ያላቸውን ምግቦች (ለምሳሌ ዳቦ፣ ፓስታ፣ ጣፋጭ ፍራፍሬዎ) ይቀንሱ። ለስኳር በሽታ ተስማሚ የሆነ የአመጋገብ መከተል ለመድሀኒቱ መስራት እና ለአጠቃላይ ጤንነት ጥሩ ነው።
እርጉዝ ሴቶች፦ በእርግዝና ግዜ የስኳር በሽታን መቆጣጠር ለእናትም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት ማርገዟን ስታውቅ መድሀኒቱን ላዘዘላት ሀኪም እንድታሳውቅ ይመከራል።
የሚያጠቡ ሴቶች፦ ይህ መድሀኒት በጡት ወተት እንዳለ ወይም እንደሌለ አይታወቅም። ስለአማራጭ መድሀኒቶች ወይም ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ ሀኪማቸውን ያማክሩ።
ሌሎች ጥንቃቄዎች
የኩላሊት በሽታ ሲኖር የሚወስዱት የመድሀኒት መጠን ሊቀነስ ይችላል። ይህን ለማወቅ በየግዜው የኩላሊት ምርመራ ሊታዘዝ ይችላል።
አሎግልፕቲን የጣፊያ ህመም (pancreatitis) ሊያባብስ ይችላል። የዚህ ህመም ምልክቶች ሀይለኛ የማያቋርጥ እና እስከጀርባ ድረስ የሚሰማ የሆድ ህመም ማቅለሽለሽ ማስታወክ እና ዘይት ያለበት የሚመስል ሰገራ ሊሆን ይችላል። ይህን መድሀኒት እየወሰደ እንዲህ ያለ ህመም የሚሰማው ሰው ለሀኪሙ እንዲያሳውቅ ይመከራል።
ይህን መድሀኒት የወሰዱ ጥቂት ሰዎች ላይ የልብ ድካም (heart failure) ታይቷል። ይህንን መድሀኒት ሲወስዱ የልብ ድካም ምልክቶችን ማወቅ ጥሩ ነው። የትንፋሽ ማጠር (በተለይ ጋደም ሲሉ የሚብስ)፣ ያልተለመደ የድካም ስሜት፣ የእግር ወይም የእጅ ማበጥ፣ የሰውነት ክብደት በፍጥነት መጨመር፣ ደረት ላይ ህመም መኖር ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ምልክቶች ከታዩ ለሀኪምዎ ይንገሩ።
ይህን መድሀኒት ሲወስዱ የቆዳ ወይንም የአይን (ነጭ ክፍል) ወደቢጫ ከተለወጠ፣ የሽንት ቀለም ከጠቆረ፣ የሰገራ ቀለም ከነጣ፣ ወይም ያልተለመደ ድካም፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ካለ ለሀኪም ያማክሩ። እነዚህ የጉበት ህመም ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪ ሀኪም የጉበት ጤንነት ለመርመር በየግዜው የላብራቶሪ ምርመራ ሊያዝ ይችላል።
ይህን መድሀኒት ሲወስዱ የመገጣጠሚያ ህመም (joint pain) ሊሰማ ይችላል። እንዲህ አይነት ህመም ካጋጠመ ለሀኪም ማማከር ጥሩ ነው።
አንዳንድ ሰዎች ለአሎግልፕቲን አደገኛ አለርጂ ሊኖራቸው ይችላል። አናፍላክሲስ (Anaphylaxis)፣ አንጂዮኢዴማ (Angioedema)፣ እና ስቲቨን ጆንሰን (Stevens-Johnson Syndrom) አጣዳፊ ህክምና የሚያስፈልጋቸው አለርጂ አይነቶች ናቸው። እነዚህ የህመም ምልክቶች መካከል አንዱ ከታየ ቶሎ ሀኪም ጋር መሄድ አስፈላጊ ነው። ዋና ዋና ምልክቶች
- ለመተንፈስ መቸገር
- የፊት የምላስ የከንፈር ወይም የጉሮሮ ማበጥ
- የቆዳ ሽፍታ እና ማሳከክ
- የቆዳ መቅላት
- ውሃ የሚቋጥር ሽፍታ
- የቆዳ መሰነጣጠቅ ሊሆን ይችላሉ።
አሎግልፕቲን ን የሚወስዱ ሰዎች የደም ግሉኮሳቸው ከሚፈለገው በታች ዝቅ ሊል ይችላል። ከሌሎቹ የስኳር በሽታ መድሀኒቶች ሲወዳደር እድሉ ዝቅተኛ ቢሆንም ምልክቶቹን እና የሚያስፈልገውን ጥንቃቄ ማወቅ ጥሩ ነው።
ሀይፓግላይስሚያ (Hypoglycemia)
የደም ግሉኮስ ሲለካ ከ70 በታች ሲሆን ወይም አንዳንድ የህመም ምልክቶች ሲታዩ የደም ግሉኮስ ከሚፈለገው በታች ነው (Hypoglycemia) ይባላል። እንደከፍተኛ የደም ግሉኮስ ሁሉ ይህ የደም ግሉኮስ በጣም ዝቅ ማለት ለጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል።
ይህን የጎን ጉዳት ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮች ውስጥ መድሀኒቱን ያለምግብ መውሰድ፣ በቂ ምግብ አለመመገብ፣ እና ሌሎች አንዳንድ መድሀኒቶች ናቸው። እንዲሁም ከ65 አመት በላይ እድሜ ያላቸው ሰዎች ለዚህ ጎን ጉዳት የበለጠ የተጋለጡ ናቸው። ምልክቶቹን ማወቅ እና ጥንቃቄ ማድረግ ጥሩ ነው።
ዋና ዋና የህመም ምልክቶች
- የረሀብ ስሜት
- የመንቀጥቀጥ ስሜት
- በላብ መጠመቅ
- ብዥታ
- የሰውነት መዛል
- ያለተለመደ ግራ መጋባት (confusion)
- ራስ ማዞር
- የልብ በሀይል መምታት፣
- እንዲሁም ከባሰ እራስን መሳት ናቸው።
እነዚህ ምልክቶች የተሰማው ሰው የሚከተሉትን ማድረግ አለበት
- ከተቻለ የደም ግልሉኮስ መለካት
- ይህ ካልተቻለ ወይም ተለክቶ የደም ግልኮስ ከ70 በታች ከሆነ ስኳርነት ያለው ምግብ ወይም መጠጥ መውሰድ። ለምሳሌ የግሉኮስ ታብሌት፣ አንድ ማንኪያ ስኳር፣ ማር፣ ከረሜላ፣ ግማሽ ብርጭቆ የብርቱካን ጭማቂ ወይም አንድ ብርጭቆ ወተት መውሰድ ይቻላል።
- ከ15 ደቂቃ በሁዋላ የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ደግሞ መለካት።
- ተለክተው ከ70 በላይ ከሆነ ቀለል ያለ ምግብ መመገብ
- ተለክተው ከ70 በታች ከሆነ ከ 1 –3 ያሉትን የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ እስኪሆን ድረስ መደጋገም።
- የስኳር በሽታዎን ለሚከታተል ሀኪምዎ መንገር አይርሱ።
መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ
ይህ መድሀኒት ሙቀት ቅዝቃዜ እና እርጥበት በሌለበት ህጻናት በማይደርሱበት ቦታ መቀመጥ አለበት።
ኩፓን
አሎግልፕቲን ከሌሎች የስኳር የስኳር በሽታ መድሀኒቶች ሲወዳደር ውድ ነው። በዲፒፒ 4 ምድብ ውስጥ ከሚገኙ መድሀኒቶች ጋር ሲወዳደር ርካሽ ነው።
ጉድ አር ኤክስ (GoodRx)
ጉድ አር ኤክስ ድረገጽ ላይ የመድሀኒቱን ስም ምን ያህል ሚሊግራም እንደሆነ እና ምን ያህል ክኒን እንደሚፈልጉ ካስገቡ በኋላ ቅናሽ የምያገኙበትን ካርድ ፕሪንት እንዲያደርጉ ይጠይቃል። ይህንን ካርድ ወደፋርማሲ ይዘው ይሂዱ። ጉድ አር ኤክስ እና ሌሎች ዲስካውንት ካርዶች ከመንግስት ኢንሹራንስ ጋር አይሰሩም። ከዛ ውጭ ግን በአሜሪካ ውስጥ ጥሩ የመድሀኒት ቅናሽ ማግኛ ዘዴ ነው።
ማጣቀሻ
- “Diabetes Mellitus.” Pharmacotherapy Handbook, by Barbara G. Wells et al., McGraw-Hill Education, 2017, pp. 161–175.
- NESINA (alogliptin) tablets, for oral use [package insert]. Deerfield, IL 60015.: Takeda Pharmaceuticals America, Inc.; 2016.
ቀን: 02/04/21
በቅርብ ግዜ የወጡ ጽሁፎች
- ስኳር በሽታ
የስኳር በሽታ በደም ውስጥ ከመጠን በላይ ግሉኮስ ሲኖር የሚፈጠር በሽታ ነው። የዚህ መንስኤ በተፈጥሮ ከጣፊያ…
- ቅድመ ስኳር በሽታ (Pre-diabetes)
በደም ውስጥ ያለ ግሉኮስ መጠን ሲጨምር ነገር ግን የስኳር በሽታን ያህል ከፍተኛ ካልሆነ ቅድመ ስኳር…
- ሲታግልፕቲን
ሲታግልፕቲን (Sitagliptin) የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ ሲታግልፕቲን የብራንድ ስም፦ ጅኑቪያ (Januvia) ምድብ፦ ዲፒፒ 4 የሚያግድ (DPP-4…