Amharic Health Information

ግላይቢውራይድ (Glyburide)

የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ ግላይቢውራይድ (Glyburide)

ምድብ፦ ሰልፎንይልዩርያ (Sulfonylurea)

የብራንድ ስም፦ ማይክሮኔስ (Micronase)፣ ዳያቤታ (Diabeta)፣ ግላይኔስ (Glynase)

ግላይቢውራይድ ለምን ይታዘዛል?

በስኳር በሽታ ህመምተኞች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል ይረዳል።

ግላይቢውራይድ እንዴት ነው የሚሰራው?

አይነት ሁለት የስኳር በሽታ ያለበት ሰው ኢንሱሊን የሚያመርተው የጣፍያ ህዋሶቹ (beta cells of pancreatic islet) ይደክማሉ። እነዚህ ህዋሶች ኢንሱሊን የማምረት አቅማቸው ዝቅተኛ ይሆናል። ኢንሱሊን ከሌለ በደም ውስጥ ያለው ግሉኮስ ወደሚያስፈልገው የሰውነት ክፍል መሄድ አይችልም። በዚህ ምክንያት በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን እየተጠራቀመ እና እየጨመረ ይሄዳል።

ግላይቢውራይድ እነዚህን የተዳከሙ እንዲሁም የተቀሩትን ጤናማ የጣፊያ ህዋሶች የተሻለ መጠን ያለው ኢንሱሊን እንዲያመርቱ ያደርጋቸዋል። ይህ ኢንሱሊን በደም ውስጥ ያለው ግሉኮስ ወደሚያስፈልገው የሰውነት ክፍል ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የደም ግሉኮስ መጠንን እንዲቀንስ ያደርገዋል።

ግላይቢውራይድ በምን መልኩ ይመረታል?

ግላይቢውራይድ በኪኒን መልኩ ተመርቶ ገበያ ላይ ይቀርባል። ብዙ ጊዜ ግላይቢውራይድ በ 1.25, በ2.5 እና በ5 ሚሊግራም (mg) መጠን ይመጣል። ግላይኔስ የሚባለው የግላይቢውራይድ ኪኒን በ1.5፣ በ3 እና በ6 ሚሊግራም (mg) መጠን ይመጣል።

ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ምንድነው?

ይህ መድሀኒት የሚሰራው ሀኪም ባዘዘው መሰረት በየእለቱ ሲወሰድ ነው።

ከመድሀኒቱ በተጨማሪ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እና አመጋገብ ማስተካከል የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋፆ አለው።

ይህ መድሀኒት የደም ግሉኮስን ያስተካክላል እንጂ የስኳር በሽታን አይፈውስም። የስኳር በሽታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ህመም ነው። የህክምናው አላማ የደም ግሉኮስን በመቀነስ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ ኩላሊት እና አይን) ላይ የሚያደርሰውን በሽታ መከላከል ነው። የደም ግሉኮስ ሲቀንስ ይህን መድሀኒት መውሰድ ማቆም የደም ግሉኮስ ተመልሶ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ የደም ግሉኮስ ቢስተካከል ወይም ጤንነት ቢሰማ እንኳን ይህን መድሀኒት ያለሀኪም ምክር ማቆም ትክክል አይደለም።

እርጉዝ ሴቶች፦ ይህ መድሀኒት በእርግዝና ግዜ ከእናት ወደፅንስ ሊተላለፍ ይችላል። ነገር ግን ይህ መድሀኒት በፅንስ ላይ ጉዳት ማድረሱን ለማወቅ የሚያስችል ሰፊ ጥናት የለም።  ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት መፀነሷን ስታውቅ መድሀኒቱን ላዘዘላት ሀኪም እንድታሳውቅ ይመከራል።

በእርግዝና ግዜ የስኳር በሽታን መቆጣጠር ለእናትም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት አስፈላጊ ነው። በእርግዝና ምክንያት ለሚመጣ የስኳር በሽታ ከሚታዘዙት ሶስት መድሀኒቶች መካከል ግላይቢውራይድ አማራጭ ነው(4)። ስለዚህ በእርግዝና ግዜ ይህ መድሀኒት ሊታዘዝ ይችላል።

የሚያጠቡ ሴቶች፦ ግላይቢውራይድ የምትወስድ እናት የጡት ወተት ውስጥ መድሃኒቱ ሊኖር ይችላል። ስለአማራጭ መድሀኒቶች ወይም ማድረግ ስላለብዎት ጥንቃቄ ሀኪምዎን ያማክሩ።

ይህ መድሀኒት የማይታዘዝላቸው ሰዎች (Contraindication)

  1. ከዚህ በፊት ይህን መድሀኒት ወስደው አደገኛ አለርጂ ያጋጠማቸው ሰዎች።
  2. አይነት አንድ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች እንዲሁም ከስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ ኪቶአሲዶሲስ (diabetic ketoacidosis) ያጋጠማቸው ሰዎች።
  3. ቦሰንተን (Bosentan) የሚባል መድሀኒት የሚወዱ ሰዎች።

የመድሀኒት መስተጋብር

ከዚህ መድሀኒት ጋር ቦሰንተን (bosentan) መውሰድ ለጉበት በሽታ ሊያጋልጥ ይችላል።

በተጨማሪ ሌሎች እንዳንድ መድሀኒቶች ከግላይቢውራይድ ጋር ሲወሰዱ የጎን ጉዳቱን ሊያባብሱት እንዲሁም የመድሀኒቱ እንዳይሰራ ሊያደርጉት ይችላሉ። ከነዚህም መካከል ያለሀኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ የህመም ማስታገሻዎች አድቪል (Advil) እና አሊቭ (Aleve) ይገኙበታል። ግልምፕራይድ እየወሰዱ አዲስ መድሀኒት ሲጀምሩ ሀኪም ወይም ፋርማሲስት በማማከር ለጎን ጉዳት (side effect) እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ ያድርጉ።

አልኮል፦ እንደብዙ መድሀኒቶች ሁሉ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ አልኮል መጠጥ መጠጣት አይመከርም።

ምግቦች፦ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ ጣፋጭ የሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ ካርቦሀይድሬት (carbohydrate) ያላቸውን ምግቦች (ለምሳሌ ዳቦ፣ ፓስታ፣ ጣፋጭ ፍራፍሬዎች) ይቀንሱ። ለስኳር በሽታ ተስማሚ የሆነ የአመጋገብ መከተል ለመድሀኒቱ መስራት እና ለአጠቃላይ ጤንነት ጥሩ ነው።

የግላይቢውራይድ አወሳሰድ

የሀኪምዎን ትእዛዝ ይከተሉ።

በቀን የመጀመሪያው የመብል ሰአት ላይ ከምግብ ጋር መውሰድ ይቻላል።

አንዳንድ ህመምተኞች በቀን ሁለት ግዜ እንዲወስዱ ሊታዘዝላቸው ይችላል።

መድሀኒቱ የሚወሰድበት ሰአት ተመሳሳይ ቢሆን ይመረጣል።

መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?

ወድያው እንዳስታወሱ ይውሰዱ። ብዙ ሰአት ካለፈ ይተውት እና በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ጊዜዎ የተለመደውን መጠን ይዋጡ። የረሱትን ጨምረው ለመዋጥ አይሞክሩ።። ለሀኪምዎ ሳያማክሩ መድሃኒት መውሰድ አያቁሙ።

የጎን ጉዳት (Side-effect)

ይህን መድሀኒት የሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች ማቅለሽለሽ፣ ቃር፣ ቆዳ ማሳከክ እና ሽፍታ ሊያመጣባቸው ይችላል። ይህ ብዙ ግዜ መድሀኒቱ ሲጀመር አከባቢ የሚሰማ ህመም ነው። መድሀኒቱ ከሰውነት ጋር ሲላመድ ይተዋል። ካልተወ ወይም ከአቅም በላይ ከሆነ ግን ለሀኪምዎ ያሳውቁ። 

ይህን መድሀኒት ከአልኮል ጋር መውሰድ ሀይለኛ የማቅለሽለሽ ስሜት ሊያመጣ ይችላል.። እንዲሁም ሌሎች የጎን ጉዳቶችን ሊያባብስ ይችላል።

ወስደው አልኮል መጠጣት ሀይለኛ የማቅለሽለሽ ስሜት ሊያመጣ ይችላል።

ይህን መድሀኒት ሲወስዱ የሰውነት ክብደት መጨመር ሊታይ ይችላል።

ስለሀይፖግላይስሚያ (Hypoglycemia) “ሌሎች ጥንቃቄዎች” በሚለው ርዕስ ስር ያንብቡ።

ለዚህ መድሃኒት የሃኪም ክትትል ያስፈልገኛል?

የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሀኪም ቤት ቀጠሮ መከታተል ያስፈልጋቸዋል። ይህ የሚደረገው

  1. የታዘዘላቸው መድሀኒት ስኳር በሽታቸውን ለመቆጣጠር እየረዳቸው መሆኑን ለማወቅ
  2. በመድሀኒቱ ምክንያት የሚመጡ የጎን ጉዳቶች እየተባባሱ እንዳልሆኑ ለማወቅ
  3. በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጡ ሌሎች ህመሞች (ለምሳሌ የኩላሊት በሽታ) ካሉ በጊዜ ለማወቅ እና የሚያስፈልገውን ህክምና ለማድረግ

በተጨማሪ የአይነቱ ሁለት የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከጊዜ በሁዋላ ጣፊያቸው ሙሉ በሙሉ ኢንሱሊን የማምረት ችሎታውን ሊያጣ ይችላል። በዚህ ጊዜ ይህ መድሀኒት ስለማይሰራ ሃኪማቸው ወደሌላ መድሀኒት ሊለውጥላቸው ይችላል። ስለዚህ የህክምና ቀጠሮዎን መከታተል ጥሩ ነው።

ሌሎች ጥንቃቄዎች

መጀመሪያ የሚታዘዘው መድሀኒት መጠን የደም ግሉኮስን ወይም ኤዋንሲን (A1C) ላያስተካክል ይችላል። ስለዚህ ሀኪም ይህን መድሀኒት በትንሽ መጠን ጀምሮ ቀስ በቀስ እየጨመረ መሄድ ይፈልግ ይሆናል።  የስኳር በሽታን መቆጣጠር እስከሚቻል ድረስ የመድሀኒቱ መጠን እያስተካከሉ መሄድ የመድሀኒቱን የጎን ጉዳት (side-effect) ለመቀነስ እና ለህመምተኛው የሚሆነውን ትክክለኛውን የመድሀኒት መጠን ለማግኘት ይጠቅማል።

ሀይፓግላይስሚያ (Hypoglycemia)፦ አንዳንድ ሰዎች ግላይቢውራይድን ሲወስዱ የደም ግሉኮሳቸው መጠን ከሚፈለገው በታች ሊወርድ ይችላል።

የደም ግሉኮስ ሲለካ ከ70 በታች ሲሆን ወይም አንዳንድ የህመም ምልክቶች ሲታዩ የደም ግሉኮስ ከሚፈለገው በታች ነው (Hypoglycemia) ይባላል። እንደከፍተኛ የደም ግሉኮስ ሁሉ ይህ የደም ግሉኮስ በጣም ዝቅ ማለት ለጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል።

ይህን የጎን ጉዳት ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮች መድሀኒቱን ያለምግብ መውሰድ፣ በቂ ምግብ አለመመገብ፣ እና ሌሎች አንዳንድ መድሀኒቶች ናቸው። እንዲሁም ከ65 አመት በላይ እድሜ ያላቸው ሰዎች ለዚህ ጎን ጉዳት የበለጠ የተጋለጡ ናቸው። ምልክቶቹን ማወቅ እና ጥንቃቄ ማድረግ ጥሩ ነው።

ዋና ዋና የህመም ምልክቶቹ የረሀብ ስሜት፣ ያለተለመደ ግራ መጋባት (confusion)፣ ራስ ማዞር፣ የሰውነት መዛል፣ የመንቀጥቀጥ ስሜት፣  በላብ መጠመቅ፣ የልብ በሀይል መምታት፣ እንዲሁም ከባሰ እራስን መሳት ናቸው።

እነዚህ ምልክቶች የተሰማው ሰው ማድረግ ያለበት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው

  1. ከተቻለ የደም ግልሉኮስ መለካት
  2. ይህ ካልተቻለ ወይም ተለክቶ የደም ግልኮስ ከ70 በታች ከሆነ ስኳርነት ያለው ምግብ ወይም መጠጥ መውሰድ። ለምሳሌ የግሉኮስ ታብሌት፣ አንድ የሻይ ማንኪያ ስኳር፣ ከረሜላ፣ ግማሽ ብርጭቆ የብርቱካን ጭማቂ ወይም አንድ ብርጭቆ ወተት መውሰድ ይቻላል።
  3. ከ15 ደቂቃ በሁዋላ የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ደግሞ መለካት።
  4. ተለክተው ከ70 በላይ ከሆነ ቀለል ያለ ምግብ መመገብ
  5. ተለክተው አሁንም ከ70 በታች ከሆነ እንደገና ጣፋጭነት ያለው ምግብ መብላት እና ወደሀኪም ቤት መሄድ።
  6. ይህ አንዴ ካጋጠመ የስኳር በሽታዎን ለሚከታተል ሀኪምዎ መንገር አይርሱ።

የኩላሊት ወይም የጉበት በሽታ ያለባቸው ሰዎች ይህንን መድሀኒት ሲወስዱ የጎን ጉዳት(side-effects) እንዳይባባስባቸው መጠንቀቅ አለባቸው። በተጨማሪ የኩላሊት ምርመራቸውን አይቶ ሀኪም መድሀኒቱን ሊለውጥ ይችላል።

የልብ ወይም የደም ስር በሽታ ላለበት ሰው ከግላይቢውራይድ የተሻለ መድሀኒት ሊኖር ይችላል። መድሀኒት ለሚያዝልዎት ሀኪም ከዚህ በፊት የልብ ወይም የደም ስር በሽታ አጋጥሞት ከነበረ መንገር አይዘንጉ።

መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ

መድሀኒት የሚቀመጥበት ቦታ ሙቀት፣ ቅዝቃዜ እና እርጥበት የማይበዛበት ህጻናት የማይደርሱበት ቦታ ነው።

ማጣቀሻ

  1. Diaßeta® (glyburide) Tablets USP [package insert]. Bridgewater, NJ 08807: sanofi-aventis U.S. LLC; 2009.
  2. “Diabetes Mellitus.” Pharmacotherapy Handbook, by Barbara G. Wells et al., McGraw-Hill Education, 2017, pp. 161–175.
  3. Glynase® PresTab® [package insert]. NY, NY 10017: Pharmacia & Upjhn Company; 2009.
  4. Management of Diabetes in Pregnancy: Standards of Medical Care in Diabetes—2021.” Diabetes Care, vol. 44, no. Supplement 1, 2020, doi:10.2337/dc21-s014.

ቀን: 01/20/2021

ኩፓኖች