Amharic Health Information

አይቢፕሮፊን (Ibuprofen)

የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ አይቢፕሮፊን (Ibuprofen)

ምድብ፦  ስቴሮይድ ነክ ያልሆነ አንቲ ኢንፍላማቶሪ መድሃኒት (Non-Steroidal Anti-Inflammatory Drugs (NSAIDs))

የሜትፎርሚን ብራንድ ስሞች አድቪል(Advil) ሞትሪን(Motrin)

አይቢፕሮፊን (Ibuprofen) ለምን ህመም ይወሰዳል?

አይቢፕሮፊን  ለቀላል ህመሞች  ማስታገሻ ሊወሰድ ይችላል። ለምሳሌ፦

  • ቁርጥማት
  • አንጓ ብግነት(አርተራይተስ)
  • የወር አበባ ህመሞች
  • ትኩሳት ለማስታገስ
  • ራስምታት
  • የጥርስ ህመም
  • ጉንፋን

አይቢፕሮፊን እንዴት ነው የሚሰራው?

ይህ መድሃኒት የሰውነት መቆጣትን (inflammation) በመቀነስ እና ከህመም ስሜት ጋር የተያያዙ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎች እንዲቀንሱ በማድረግ ህመምን  ያስታግሳል።

አይቢፕሮፊን በምን መልኩ ተመርቶ ይታሸጋል?

  • በፈሳሽ መልክ የሚወሰድ
  • በአፍ የሚዋጥ ክኒን

አይቢፕሮፊን መውሰድ የሌለባቸው ሰዎች

  • ከዚህ በፊት ለአይቢፕሮፊን ወይም ለአስፕሪን የሰውነት መቆጣት (allergy ) ያሳዩ ሰዎች።

የአይቢፕሮፊን አለርጂ ምልክቶች የሚያሳክክ ሽፍታ፣ የፊት ማበጥ፣ ለመተንፈስ መቸገር፣ የቆዳ መቅላት፣ የቆዳ ውሃ መያዝ እና ሌሎችም ሊሆኑ ይችላሉ።

  • እርጉዝ ሴቶች ወይም ለመጸነስ ሃሳብ ያላቸው ሴቶች።
  • የሚከተሉትን መድሃኒቶች የሚወስዱ ሰዎች
    • የደም ማቅጠኛ (anticoagulants) ለምሳሌ ወርፈሪን(warfarin)
    • ስቴሮይድ(steroid) መድሃኒት የሚወስዱ። የስቴሮይድ መድሃኒት ምሳሌዎች ሜድሮል(Medrol) እና ፕሪድኒሶን (Prednisone) ናቸው።
    • አስፕሪን(Aspirin) የሚወስዱ ሰዎች።
  • እንዲሁም የሚከተሉት ህመሞች ያለባቸው ሰዎች ያለሀኪም ፍቃድ አይቦፕሮፊን መውሰድ የለባቸውም
    • አስም
    • ከፍተኛ ደም ግፊት
    • የልብ በሽታ
    • የጉበት በሽታ
    • የኩላሊት በሽታ
    • ከደምስር ጋር የተየያዘ በሽታ (ለምሳሌ ስትሮክ)
    • የጨጓራ ሀመም
    • ከዚህ በፊት በጨጓራ መቁሰል ወይም መድማት ያጋጠማቸው ሰዎች

የአይቢፕሮፊን ትክክለኛ አወሳሰድ

ለቀላል ህመም ወይም ትኩሳት ለማስታገስ

  • አንድ የሁለት መቶ ሚሊግራም(200 mg) ክኒን ይውሰዱ። ህመም ወይም ትኩሳት ካልታገሰ ከአራት እስከስድስት ሰአት ባለው ግዜ ውስጥ ደግመው መውሰድ ይችላሉ።
  • አንድ የሁለት መቶ ሚሊግራም ክኒን ህመምዎን የማያስታግስ ከሆነ ሁለት ክኒን መውሰድ ይቻላል።
  • ያለዶክተር ትእዛዝ በሀያአራት ሰአት ግዜ ውስጥ ከስድስት ኪኒን በላይ አይውሰዱ። ህመም ወይም ትኩሳት የማይቀንስ ከሆነ ሀኪምዎን ያማክሩ።

ይህን መድሃኒት ከምግብ ጋር ወይም ከወተት ጋር ይውሰዱ።

ለረጅም ግዜ አይቢፕሮፊን መውሰድ ለጨጓራ እና ለልብ ህመሞች ሊያጋልጥ ይችላል። ስለዚህ ለቀላል ህመሞች አይቢፕሮፊን ሲወስዱ ትንሹን መጠን ለአጭር ግዜ ብቻ ይውሰዱ።

በዚህ መድሃኒት ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች

ይህ መድሃኒት የሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች የሆድ ህመም (የጨጓራ ህመም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ የሆድ ድርቀት፣ የሆድ መወጠር ስሜት፣ እና ጋዝ) ሊሰማቸው ይችላል። ይህን ለመከላከል ሁል ግዜ መድሃኒቱን ከምግብ ጋር መውሰድ ይመከራል። በተጨማሪ በተቻለ መጠን ለአጭር ግዜ እና ትንሹን መጠን መውሰድ ጥሩ ነው። እንዲሁም የራስ ምታት፣ ሽፍታ፣ ጆሮ ላይ ጭው የሚል ድምጽ መሰማት፣ ራስ ማዞር እንዲሁም የምግብ ፍላጎት መቀነስ ሊከሰት ይችላል።

መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ

መድሃኒትዎን፤ ሙቀት እና ቅዝቃዜ የማይበዛበት፤  ደረቅ ቦታ ያስቀምጡ። መድሃኒትን መታጠቢያ ቤት ማስቀመጥ አግባብ  አይደለም። ህጻናት እና የቤት እንስሳት የማይደርሱበት ቦታ ያስቀምጡ።

የከፍተኛ ጥንቃቄ (FDA blackbox)

አይቢፕሮፊንን ጨምሮ ሁሉም ስቴሮይድ ነክ ያልሆኑ አንቲ ኢንፍላማቶሪ መድሃኒቶች ለልብ እና ደምስር በሽታዎች ሊያጋልጡ ይችላሉ። እነዚህ የልብ እና ደምስር በሽታዎች የደም መጓጎል ድንገተኛ የልብ ህመም እና ስትሮክን ያጠቃልላሉ።

እነዚህ ህመሞች ከዚህ በፊት ያጋጠመው ሰው ወይም ለእነዚህ በሽታዎች የሚያጋልጥ ተጨማሪ ህመም ወይም የቤተሰብ ታሪክ ያለበት ሰው አይቢፕሮፊን ሆነ በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ መድሃኒቶችን ያለሀኪም ትእዛዝ መውሰድ የለበትም።

አይቢፕሮፊን እና ተመሳሳይ መድሃኒቶች ለጨጓራ እና ለአንጀት ህመም፣ መቁሰል(ulceration)፣ እና መድማት(bleeding)፣ አልፎም ለመቀደድ(perforation) ሊያጋልጥ ይችላል። እድሜያቸው የገፋ (ከ65 አመት እድሜ በላይ) ለዚህ የተጋለጡ ናቸው።

ማጣቀሻ

ማጣቀሻ
Ibuprofen Tablets [package insert]. Glasgow, KY 42141: Ameal Pharmaceuticals Corp.; 2014.
Motrin®Ibuprofen Tablets [package insert]. NY, NY 10017: Division of Pfizer Inc,.; 2007.

ቀን: 07/23/20