Amharic Health Information

ትኩሳት በህጻናት ላይ

ትኩሳት ምንድን ነው?

ትኩሳት ሰውነት ከጎጂ ባክቴርያዎች እና ሌሎች ተውሳኮች ራሱን በሚከላከልበት ጊዜ የሚፈጠር የሰውነት ሙቀት መጨመር ነው። ጤነኛ የሆነ ህጻን የሰውነት ሙቀት 97 እስከ 100.4 ዲግሪ ፋራናይት(36.1 እስከ 38 ዲግሪ ሴልሸስ) ነው።

የሰውነት ሙቀት እንዴት መለካት ይቻላል?

ትኩሳት በህጻናት ላይ ሲኖር መጀመሪያ መደረግ ያለበት ነገር የህጻኑን የሙቀት መጠን በቴርሞ ሜትር ለክቶ ማወቅ ነው።  ልጅ ያለው ሰው ቴርሞ ሜትር በቤቱ ቢኖረው መልካም ነው። ዲጂታል ቴርሞሜትር በዋጋ ተመጣጣኝነትም ሆነ ለአጠቃቀም ቅለት ከሌሎቹ የቴርሞሜትር አይነቶች የተሻለ ነው።

የህጻናትን ሙቀት ለመለካት መጠቀም የሌለብዎ ቴርሞሜትር አይነቶች፦

  1. ከጠርሙስ የተሰራ ቴርሞሜትር፦ ከተሰበረ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
  2. በሜርኩሪ የሚሰራ ቴርሞሜትር፦ ተሰብሮም ሆነ በሌላ መንገድ ሜርኩሪው ወደሰውነት ከገባ የመርዝነት ባህሪ ይኖረዋል።  

የሰውነትን የሙቀት መጠን ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች መለካት ይቻላል። ከምላስ በታች፣ ከብብት፣ ከጆሮ፣ ከግምባር እና ከፊንጢጣ ትኩሳትን መለካት የተለመዱ መንገዶች ናቸው። ህጻኑ ከምላሱ ስር የቴርሞ ሜትሩን ጫፍ አፍኖ መያዝ የሚችል ከሆነ ከምላስ በታች ትኩሳትን መለካት የተሻለ መንገድ ነው። ካልሆነ ግን ከብብት ሙቀትን መለካት ይቻላል። ከጆሮ እና ከግምባር መለካት ትክክለኛ የሙቀት መጠን ላይሰጥ ይችላል።

measuring body temperature

ህጻኑ ከሶስት ወር በታች ከሆነ ከፊንጢጣ የሙቀት መጠንን መለካት በህክምና ባለሙያዎች የሚመከረው መንገድ ነው። የልጅዎትን ሙቀት መጠን በዚህ መልኩ መለካት ከፈለጉ ህጻኑ እንዳይጎዳ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያድርጉ። በብብት የለኩትን የሙቀት መጠን ለማረጋገጥ ቢጠቀሙበት የተሻለ ነው።

ከፊንጢጣ የሙቀት መጠንን ለመለካት፦

  1. የቴርሞሜትሩን ጫፍ ሞቅ ባለ ውሃ አጥበው በሚገባ ያድርቁት።
  2. የቴርሞ ሜትሩን ጫፍ ቫዝሊን ይቀቡት።
  3. ህጻኑን በሆዱ ያስተኙት። ድንገት እንዳይንቀሳቀስ ጀርባውን በአንድ እጅዎ ይዘው የቴርሞ ሜትሩን ጫፍ፤ ግማሽ ኢንች ያህል ወደፊንጢጣው ያስገቡት እና ለአንድ ደቂቃ ያቆዩት (ቴርሞ ሜትሩ ዲጂታል ከሆነ “ቢፕ” የሚል ድምጽ ያሰማል።)
  4. ወድያው ውጤቱን ያንብቡ።
  5. ቴርሞ ሜትሩን በውሃ እና በሳሙና ማጠብ አይርሱ።
Measuring infant temprature
በዚህ ሁኔታ የአራስ ልጅን ሙቀት መለካት ይቻላል

በትኩሳት ምክንያት ወደሃኪም ቤት መሄድ የሚያስፈልገው መቼ ነው?

አንድ ህጻን በትኩሳት ምክንያት ወደሃኪም ቤት መውሰድ የሚያስፈልግበት ጊዜ እንደህጻኑ እድሜ፤ ሌሎች ምልክቶች፤ እንዲሁም የትኩሳት መጠን ይለያያል።  አንድ ህጻን፦

  • ከፊንጢጣ በተለካ ሙቀት
    • እድሜው ከ3 ወር በታች ሆኖ ሙቀቱ 100.4 ዲግሪ ፋራናይት(38 ዲግሪ ሴልሸስ) ከሆነ
    • እድሜው ከ3 – 6 ወር ሆኖ ሙቀቱ 101 ዲግሪ ፋራናይት(ዲግሪ ሴልሸስ) ከሆነ
    • እድሜው ከ6 ወር በላይ ሆኖ ሙቀቱ 103 ዲግሪ ፋራናይት(39.4 ዲግሪ ሴልሸስ ) ከሆነ
  • የትኛውም እድሜ ላይ የሆነ ልጅ ከየትኛውም ቦታ የተለካው (ከግምባሩ ቢሆን እንኳ) 104 ዲግሪ ፋራናይት(°F) ወይም 40 ዲግሪ ሴልሸስ(°C) ከሆነ
  • ልጁ ለሰባት ቀን ያህል ካልተሻለው፤ ሰውነቱን የሚያሳክከው ሽፍታ ካለበት፣ ውሃ እና ምግብ አልቀምስም እንዲሁም ጡት አልጠባም ካለ፣ እንደሚጥል በሽታ(seizure) የሚያንቀጠቅጠው ከሆነ እና ሌሎች ተጓዳኝ ምልክቶች ካሉት ወደሃኪም መወሰድ ይኖርበታል።

የህጻኑ ሙቀት መጠን ከ100.4 ዲግሪ ፋራናይት(38 ዲግሪ ሴልሸስ) በታች ከሆነ እና ሌሎች  ምልክቶች ከሌሉ ሀኪም ቤት መውሰድ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ትኩሳቱ ህጻኑን ካስጨነቀው (ምቾት ከነሳው) የትኩሳት መድሃኒት ከመጠቀምዎ በፊት የሚከተሉትን መንገዶች ይሞክሩ

  • በርጥብ ፎጣ ግንባሩን/ማጅራቱን ማቀዝቀዝ
  • ቀለል ያለ ልብስ ማልበስ
  • ሰውነቱን ቀዝቀዝ ባለ ውሃ ማጠብ

በትኩሳት ጊዜ ከሰውነት ብዙ ውሃ ስለሚወጣ ያንን ለመተካት ለህጻኑ በቂ ፈሳሽ እንዲጠጣ ማበረታታት አስፈላጊ ነው። ትኩሳቱ የማይበርድ ከሆነ እና ህጻኑን ካስጨነቀው ከፋርማሲ በሚገዙ መድሃኒቶች ትኩሳትን መቀነስ ይቻላል።

ለትኩሳት የሚሰጡ መድሃኒቶች

ትኩሳት ለማብረድ ያለዶክተር ትእዛዝ የሚሸጡ መድሃኒቶችአሲታሚኖፍን (acetaminophen/Tylenol/ Motrin) እና  አይቦፕሮፍን (ibuprofen/Advil/) ናቸው።

1. አሲታሚኖፍን(Acetaminophen/Tylenol)

አሲታሚኖፊን ለልጆች የተሻለ የትኩሳት ማስታገሻ ነው። ይህ መድሃኒት በፈሳሽ  መልክ በተለያዩ ጣእሞች ተዘጋጅቶ ይመጣል። አንዴ አሲታሚኖፍን  ከሰጡት በሃላ ህጻኑ ከተሻለው ደግሞ መስጠት አያስፈልግም። ካልተሻለው ግን  ከአራት እስከስድስት ሰአት ባለው ጊዜ ውስጥ ደግመው መስጠት ይችላሉ። በሃያአራት ሰአት ጊዜ ውስጥ ከአምስት ጊዜ በላይ መሰጠት የለበትም። ከተጠቀሰው በላይ አሲታምኖፍን ለህጻናት መስጠት የጉበት በሽታ ሊያመጣ ይችላል። ስለዚህ ልጅዎ ከሚመከረው በላይ ከላይ የተጠቀሰውን መድሃኒት የወሰደ ከመሰለዎ ወደሆስፒታል ይውሰዱት።

 

    • ከሁለት አመት እድሜ በታች ለሆኑ ህጻናት ያለሃኪም ትእዛዝ ይህን መድሃኒት መሰጠት የለበትም።

 

ምን ያህል እንደሚሰጡ ለማወቅ፤ የመድሃኒቱ ብልቃጥ ላይ የተጠለጠፈው ወረቀት(ካርቶኑ) ላይ ያለውን ትእዛዝ (dosing or directions )  ፈልጉ።  የልጅዎትን ክብደት ካወቁት፤ በክብደቱ መሰረት ይስጡት።  ትኩሳት ያለበት ልጅ በቅርብ ጊዜ ተመዝኖ የማያውቅ ከሆነ ግን በእድሜው መሰረት ምን ያህል ሚሊ ሊትር(mL) እንደሚሰጡት ይመልከቱ። የተሻለው መንገድ የመድሃኒቱን መጠን በክብደት መሰረት መመጠን ስለሆነ የልጅዎን ክብደት ማወቅ ጠቃሚ ነው። ካርቶኑ ላይ በተጻፈው መጠን መሰረት በስሪንጅ ወይም ከመድሃኒቱ ጋር በሚመጣው ትንሽ መመጠኛ ይለኩ።

2. አይቦፕሮፍን (Ibuprofen/Advil/Motrin)

እንደአሲታምኖፍን ሁሉ ለልጆች የሚሰጠው አይቦፕሮፊን በፈሳሽ መልክ በተለያዩ ጣእሞች ተዘጋጅቶ ይመጣል።

  • ይህ መድሃኒት ከስድስት ወር እድሜ በታች ላሉ ህጻናት መስጠት የተከለከለ ነው።
  • ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት እድሜ ላሉ ህጻናት ያለሀኪም ትእዛዝ መስጠት አይመከርም።
  • ልጅዎ ከሁለት አመት በላይ ከሆነ እና የኩላሊት ወይም የልብ በሽታ ከሌለበት አይቢፕሮፊን መስጠት ይቻላል።

እንደሌሎች ማስታገሻ መድሃኒቶች ሁሉ አንድ ጊዜ አይቦፕሮፍን ተሰጥቶት የህጻኑ ትኩሳት ከበረደ መድገም አያስፈልግም። ካልተሻለው ግን ከስድስት እስከ ስምንት ሰአት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደገና መስጠት ይቻላል። ነገር ግን በሃያ አራት ሰአት ጊዜ ውስጥ ከአራት ጊዜ በላይ መስጠት አይመከርም።

የዚህ መድሃኒት አመጣጠን ከአሲታሚኖፍን ጋር ተመሳሳይ ነው። ምን ያህል እንደሚሰጡት ለማወቅ የመድሃኒቱ ብልቃጥ ላይ የተጠለጠፈው ወረቀት ወይም ካርቶኑ ላይ ያለውን ትእዛዝ(dosing or direction) ይፈልጉ።  የልጅዎትን ክብደት ካወቁ በክብደቱ መሰረት ይስጡት።  በቅርብ ጊዜ ተመዝኖ የማያውቅ ከሆነ ግን በእድሜው መሰረት ምን ያህል ሚሊ ሊትር(mL) እንደሚሰጡት ይመልከቱ። የህክምና ባለሙያዎች የሚመክሩትና የተሻለው መንገድ የመድሃኒቱን መጠን በክብደት መሰረት መመጠን ስለሆነ የልጅዎን ግዜያዊ ክብደት ማወቅ ጠቃሚ ነው

ለህጻናት መድሃኒት ሲሰጡ ማድረግ ያለብዎት ጥንቃቄ

1. መድሃኒት ለመለካት ተገቢ መመጠኛ ይጠቀሙ

አንዳንድ ሰዎች ለህጻናት የሚሰጥ ፈሳሽ መድሃኒት ለመለካት የቤት ማንኪያ ይጠቀማሉ። ይህ ትክክል አይደለም። የቤት ማንኪያዎች የሚይዙት መጠን የተለያየ ስለሆነ ልጁ ከሚገባው በላይ ወይም ከሚገባው በታች መድሀኒት ሊሰጠው ይችላል። መድሃኒቱ መለካት ያለበት ከመድሃኒቱ ጋር ከሚመጣ ትንሽ ስኒ ይሚያክል ፕላስቲክ ወይም ለፈሳሽ መድሃኒት መለኪያ ተብሎ በሚዘጋጅ ሲሪንጅ ነው።

ፈሳሽ መድሃኒቶችን ለመለካት ለዚህ አገልግሎት የተሰሩ መመጠኛዎችን ይጠቀሙ።
2. መድሃኒትን ከምግብ ጋር ቀላቅሎ ስለመስጠት

አንዳንድ ልጆች መድሃኒት እሺ ብለው አይወስዱም። ወላጆች ይህንን ችግር ለመፍታት መድሃኒቱን በምግብ ደባልቀው ሊሰጧቸው ይሞክራሉ። ይህንን ማድረግ የአይቢፕሮፊንንም ሆነ የአሲታሚኖፊንን መድሃኒትነት አይቀንስም። ነገር ግን ህጻኑ መድሃኒቱ የተደባለቀበትን ምግብ ጥቂት በልቶ ከተወው ከቀረው ምግብ ጋር የተወሰነ መድሃኒት ስለሚቀር የሚያስፈልገውን የመድሃኒት መጠን አያገኝም። መድሃኒቱን በምግብ ደባልቆ ከመስጠት በፊት ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ጥሩ ነው። ይህን ማድረግ ከፈለጉ፤ በትንሽ (ከአንድ ማንኪያ ባልበለጠ)ጁስ ወይም አፕልሶስ(applesauce) ውስጥ መደባለቅ ይቻላል።

3. የጉንፋን መድሃኒቶች ውስጣቸው የትኩሳት መድሃኒት ሊኖራቸው ይችላል

ለልጅዎ የትኩሳት መድሃኒት ሲሰጡት ሌላ መደረግ ያለብት ጥንቃቄ አለ። ይኸውም አንዳንድ የሳል እና የጉንፋን መድሃኒቶች ውስጥ አሲታሚኖፊን ወይም አድቪል ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ የልጆች የጉንፋን መድሃኒት (Triaminic Children’s) በውስጡ አሲታሚኖፊን አለው። ስለዚህ ለልጅዎ ተጨማሪ የትኩሳት መድሃኒት መስጠት የለብዎትም። ይህንን ማድረግ ልጁን ከሚገባው በላይ መድሃኒት በሰውነቱ እንዲኖር ያደርገዋል። መድሃኒት ሲበዛ ሰውነትን ይጎዳልና ጥንቃቄ ያድርጉ።

3. አይቢፕሮፊን እና አሲታሚኖፊን እያፈራረቁ መስጠት የተለየ ጥቅም የለውም

ለልጆች በሚሰጥ የትኩሳት እና የህመም ማስታገሻ መድሃኒት ላይ ተደጋግሞ የሚነሳው ጥያቄ “አይቢፕሮፊን እና አሲታሚኖፊን እያፈራረቁ መስጠት ጥሩ ነው ወይ?” የሚለው ነው። በዚህ በኩል የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት እንዲህ ማድረግ ምንም አይነት የተለየ ጥቅም የለውም። ነገር ግን በአመጣጠን ላይ ስለሚያሳስት ህጻናቶቹን ሊጎዳቸው ይችላል። ስለዚህ ከሁለት አንዱን መርጦ መጠቀም የተሻለ ይሆናል።

4. ለህጻናት እና ለትልቅ ሰው የሚሰጠው የትኩሳት መድሃኒት የተለያየ ነው

ለህጻናት እና ለትልቅ ሰው የሚሰጠው የትኩሳት መድሃኒት ተመሳሳይ አይደለም። ስማቸው አንድ አይነት ቢሆን እንኳን በተመሳሳይ ሚሊሊትር(mL) ውስጥ ያለው የመድሃኒት መጠን ስለሚለያይ፤ የትልቅ ሰው ማስታገሻ መድሃኒት ለህጻናት አይሰጥም።

5. አስፕሪን ለህጻናት እና ለታዳጊ ልጆች አይሰጥም

አስፕሪን(aspirin) ሌላ ትኩሳት የመቀነስ ችሎታ ያለው መድሃኒት ነው። ነገር ግን እድሜያቸው ከአስራስድስት አመት በታች ለሆኑ ልጆች መስጠት አጥብቆ የተከለከለ ነው። ትኩሳቱን የሚያመጣው እንደጉፋን ያለ የቫይረስ ህመም ሊሆን ይችላል። የቫይረስ ህመም ያለባቸው ህጻናት (እያገገሙ ያሉ ወይንም ደግሞ ያለህመም በውስጣቸው ቫይረስ ያለ ቢሆን እንኳን) አስፕሪን ሲወስዱ ሬይስ ሲንድሮም(Reye’s syndrome) የሚባል በሽታ ሊያመጣባቸው ይችላል። ስለዚህ ሃኪም ካላዘዘ በስተቀር፤ ከአስራስድስት አመት በታች ላለ ህጻናት እና ታዳጊ ልጆች አስፕሪን መስጠት የተከለከለ ነው።