Amharic Health Information

ሰማግሉታይድ

የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ ሰማግሉታይድ (Semaglutide)

ብራንድ ስም፦ኦዘምፒክ (Ozempic) ራይበልሰስ (Rybelsus)

ምድብ፦ ጂኤልፒ 1 አይነት (GLP-1 Agonist)

ሰማግሉታይድ ለምን ይታዘዛል?

ሰማግሉታይድ  በአይነት ሁለት ስኳር በሽታ ህመምተኞች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል ይረዳል።

ሰማግሉታይድ በምን መልኩ ይመረታል?

ይህ መድሀኒት በኪኒን መልኩ (ራይበክሰስ) እና በመርፌ መልኩ (ኦዘምቢክ) ይመረታል።

  1. ራይበልሰስ በ3 በ7 እና በ14 ሚሊግራም በአፍ የሚዋጥ ኪኒን መልኩ ይመረታል።
  2. ኦዘምፕክ
    • 0.25 ወይም 0.5 ሚሊግራም በአንድ ጊዜ መስጠት በሚችል ፔን መልኩ እና
    • 1 ሚሊግራም በአንድ ጊዜ መስጠት በሚችል ፔን መልኩ ይመረታል።

ሰማግሉታይድ እንዴት ነው የሚሰራው?

ሰማግሉታይድ በሰውነት ውስጥ የኢንሱሊንን መጠን በመጨመር እና የግሉካንን መጠን በመቀነስ የደም ግሉኮስን ያስተካክላል።

ሰማግሉታይድ በተፈጥሮ ሰውነት ውስጥ የሚገኘውን ጂኤልፒ-1 እንዲመስል ተደርጎ የተሰራ መድሀኒት ነው። ጂኤልፒ-1 በአንጀት ከሚገኙ ኢንክሪቲን ከሚባሉ ሆርሞኖች መካከል አንዱ ሲሆን የሚጠቅመው ምግብ ከተበላ ብኋላ ከፍ ያለ የደም ግሉኮስን  ለማስተካከል ነው። ጂኤልፒ 1 የሚሰራው በሰውነት ውስጥ ከፍተኛ የግሉኮስ መጠን ሲኖር ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ ጂኤልፒ-1 በብዛት ቢኖር እንኳን የደም ግልኮስን የበለጠ ዝቅ አያደርግም።

ጂኤልፒ-1 የደም ግሉኮስን የሚቆጣጠረው አንድም ጣፊያ የኢንሱሊን ምርቱን እንዲጨምር በማድረግ ደግሞም የግሉካጎን ምርቱን እንዲቀንስ በማድረግ ነው። የኢንሱሊን መጠን መጨመር በደም ያለውን የግሉኮስ መጠን ይቀንሳል። የግሉካጎን መጠን መቀነስ ደግሞ በግላይኮጅን መልክ ተከማችቶ የሚቀመጠውን ግሉኮስ ወደደም ዝውውር እንዳይገባ ያደርገዋል። ምግብ ከተበላ ከጥቂት ሰአት በኋላ ጂኤልፒ 1 እና ሌሎች ኢንክሪቲኖች በዲፒፒ 4 ኢንዛይም ይሰባበራሉ። በዲፒፒ 4 የተሰባበሩ ኢንክሪቲኖች (ጂኤልፒ-1 ን ጨምሮ) የደም ግሉኮስን ማስተካከል አይችሉም።

ሰማግሉታይድ የሚሰራው በተፈጥሮ ከሚገኘው ጂኤልፒ-1 ጋር በተመሳሳይ መንገድ ነው። ነገር ግን በተፈጥሮ እንደሚገኘው ጂኤልፒ-1 በዲፒፒ 4 አይሰባበርም። ስለዚህ በሰውነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቆየት እና የደም ግሉኮስን ማስተካከል ይችላል።

በተጨማሪ ጂኤልፒ 1 የምግብ መንሸራሸርን ያዘገያል። ይህም የሆድ መሙላት ወይም የመጥገብ ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል። በዚህ ምክንያት በምግብ መልኩ ወደሰውነት የሚገባው የግሉኮስን መጠን ይቀንሳል።

የሰማግሉታይድ አወሳሰድ

1. ራይበልሰስ
  • የሀኪም ትእዛዝ ይከተሉ።
  • ከቁርስ ሰላሳ ደቂቃ በፊት በግማሽ ብርጭቆ ውሀ ይዋጣል። መድሀኒቱን ከተዋጠ በኋላ ለ30 ደቂቃ ምግብ መብላት የሚጠጣ ነገር መጠጣት ወይም ሌላ መድሀኒት መውሰድ መድሀኒቱ በደንብ እንዳይሰራ ያደርገዋል።
  • ኪኒኑን መቁረጥ መፍጨት ወይም ማኘክ ጥሩ አይደለም።
2. ኦዘምፒክ
  • የሀኪም ትእዛዝ ይከተሉ።
  • ኦዘምቢክ በቆዳ ስር በሳምንት አንድ ጊዜ የሚወጋ መድሀኒት ነው።
  • በቀን በማንኛውም ሰአት መወጋት ይቻላል። ለማስታወስ እንዲመች በየሳምቱ በተመሳሳይ ሰአት መውሰድ ይመከራል።
  • ምግብ ቢበሉም ባይበሉም ኦዘምቢክን መውሰድ ይቻላል።
  • የሚወጋበት ቦታ ሆድ ክንድ ወይም ታፋ ላይ ብቻ መሆን አለበት። የሚወጋበት ቦታ መዟዟር አለበት። ማለትም ዛሬ መድሀኒት የሚወጋበት ቦታ ትናንት ከተወጋበት አጠገብ መሆን የለበትም።
  • ይህ መድሀኒት ከሌላ የሚወጉ መድሀኒቶች ጋር መቀላቀል የለበትም።
  • ኢንሱሊንና ሰማግሉታይድ አጠገብ ለአጠገብ መወጋት የለበትም።

(የኦዘምፒክ (ሰማግሉታይድ) ፔን አጠቃቀም በዝርዝር ለማየት ወደጽሁፉ መጨረሻ “የሰማግሉታይድ ፔን አጠቃቀም” የሚለውን ርእስ ይመልከቱ)

መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?

ራይበልሰስ፦

የረሱትን የራይበልሰስ ክኒን ይተውት እና በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ጊዜ የተለመደውን መጠን ይውሰዱ። የረሱትን ጨምረው ለመውሰድ አይሞክሩ።

ኦዘምቢክ፦

መድሀኒት የመውሰጃ ቀን አምስት ቀን እስካላለፈው ድረስ ወድያው እንዳስታወሱ ይውሰዱ። አምስት ቀን ካለፈው ግን ይተውት እና በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ጊዜ የተለመደውን መጠን ይውሰዱ። የረሱትን ጨምረው ለመውሰድ አይሞክሩ።

የሰማግሉታይድ የጎን ጉዳት (Side-effect)

ይህን መድሀኒት የሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች የሚከተሉት የጎን ጉዳቶች ሊያጋጥማቸው ይችላል

  • ማቅለሽለሽ
  • ማስታወክ
  • ተቅማጥ
  • የሆድ ድርቀት
  • የሆድ ህመም
  • የምግብ አለመፈጨት ወይም አለመንሸራሸር ችግር
  • ድካም
  • መድሀኒት የተወጋበት ቦታ ህመም
  • የማዞር ስሜት

እነዚህ የጎን ጉዳቶች ብዙ ጊዜ መድሀኒቱ ሲጀመር አከባቢ ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን መድሀኒቱ ከሰውነት ጋር ሲላመድ ይተዋሉ። ካልተወ ወይም ከአቅም በላይ ከሆነ ግን ለሀኪም ያማክሩ። 

ለዚህ መድሃኒት የሃኪም ክትትል ያስፈልገኛል?

የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሀኪም ክትትል ያስፈልጋቸዋል። ይህም የሚደረገው

  1. የታዘዘላቸው መድሀኒት የደም ግሉኮሳቸውን በመቆጣጠር ያመጣውን ውጤት ለማወቅ
  2. በመድሀኒቱ ምክንያት የሚመጣ የጎን ጉዳት ካለ ለማወቅ
  3. በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጣ ሌላ ህመም (ለምሳሌ የኩላሊት በሽታ) ካለ በጊዜ ለማወቅ እና የሚያስፈልገውን ህክምና ለማድረግ ነው።

ሰማግሉታይድን ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ምንድነው?

ይህ መድሀኒት የሚሰራው ሀኪም ባዘዘው መሰረት በየእለቱ ሲወሰድ ነው።

ከመድሀኒቱ በተጨማሪ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግና አመጋገብ ማስተካከል የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋፆ አለው።

ይህ መድሀኒት የደም ግሉኮስን ያስተካክላል እንጂ የስኳር በሽታን አይፈውስም። የስኳር በሽታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ህመም ነው። የህክምናው አላማ የደም ግሉኮስን በመቀነስ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ ኩላሊት እና አይን) ላይ የሚያደርሰውን በሽታ መከላከል ነው። የደም ግሉኮስ ሲቀንስ ይህን መድሀኒት መውሰድ ማቆም የደም ግሉኮስ ተመልሶ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ የደም ግሉኮስ ቢስተካከል ወይም ጤንነት ቢሰማ እንኳን ይህን መድሀኒት ያለሀኪም ትእዛዝ ማቋረጥ አይመከርም።

ይህ መድሀኒት የማይታዘዝላቸው ሰዎች (Contraindication and limitations)
  1. ከዚህ በፊት ይህን መድሀኒት ወስደው አደገኛ የሰውነት መቆጣት (አደገኛ አለርጂ) ያጋጠማቸው ሰዎች
  2. በቤተሰብ ወይም ራሳቸው የታይሮይድ እጢ (thyroid tumor) ያለባቸው ሰዎች
  3. አይነት አንድ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች
  4. ከስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ ኪቶአሲዶሲስ (diabetic ketoacidosis) ያጋጠማቸው ሰዎች ናቸው።
የመድሀኒቱ መስተጋብር (Drug Interaction)

አልኮል፦ እንደብዙ መድሀኒቶች ሁሉ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ አልኮል መጠጥ መጠጣት አይመከርም።

እርጉዝ ሴቶች፦ ይህ መድሀኒት በጽንስ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። እርጉዝ ሴቶች ሰማግሉታይድ መውሰድ የለባቸውም። በተጨማሪ ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት ልጅ ለመውለድ እቅድ ካላት ከመጸነሷ ሁለት ወር ቀደም ብላ ይህንን መድሀኒት ላዘዘላት ሀኪም እንድታማክርና መድሀኒቱን እንድታስቀይር ይመከራል። በእርግዝና ግዜ የስኳር በሽታን መቆጣጠር ለእናትም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት ከተቻለ ለመጸነስ ስታስብ ካልሆነም እርጉዝ መሆኗን ስታውቅ  መድሀኒቱን ላዘዘላት ሀኪም እንድታሳውቅ ይመከራል።

የሚያጠቡ ሴቶች፦ ለሚያጠቡ ሴቶች ከሰማግሉታይድ የተሻለ መድሀኒት ሊኖር ይችላል። ሚያጠቡ ሴቶች ይህን መድሀኒት ከመውሰዳቸው በፊት ሀኪማቸውን ያማክሩ።

ምግቦች፦ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ ጣፋጭ የሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ ካርቦሀይድሬት (carbohydrate) ያላቸውን ምግቦች (ለምሳሌ ዳቦ፣ ፓስታ፣ ጣፋጭ ፍራፍሬዎች) ይቀንሱ። ለስኳር በሽታ ተስማሚ የሆነ አመጋገብ መከተል ለመድሀኒቱ መስራት እና ለአጠቃላይ ጤንነት ጥሩ ነው።

ሌሎች ጥንቃቄዎች

የጎን ጉዳቶችን ለመቀነስና ሰውነትን ለማለማመድ ሀኪም በትንሽ የመድሀኒት መጠን ጀምሮ እየጨመረ እንዲሄድ ያደርጋል። ብዙ ጊዜ ራይበልሰስ ሲጀምሩ 3 ሚሊግራም በቀን አንዴ ለአንድ ወር ይጀመርና ወደ 7 ሚሊግራም በቀን አንዴ እንዲወስዱ ይደረጋል። ሀኪም በላብራቶሪ ውጤት ላይ ተመርኩዞ የመድሀኒቱን መጠን የበለጠ ሊጨምር ይችላል። ኦዘምፒክ የሚታዘዝላቸውም ሰዎች እንዲሁ በ0.25 ሚሊግራም በሳምንት አንዴ ለአንድ ወር ተጀምሮ የሚወስዱት የመድሀኒት መጠን ወደ 0.5 ሚሊግራም በሳምንት አንድ ጊዜ እንዲወስዱ ይደረጋል።  ይህ የመድሀኒት መጠን እንደታካሚው የደም ግሉኮስ ወደ አንድ ሚሊግራም በሳምንት አንዴ ሊቀየር ይችላል። 

የታይሮይድ እጢ:- ጥቂት ይህንን መድሀኒት የወሰዱ ሰዎች የታይሮይድ እጢ(thyroid tumer) አጋጥሟቸዋል። ይህ የጎን ጉዳት ያጋጠማቸው ሰዎች በቤተሰብ ወይም ራሳቸው የታይሮይድ እጢ የነበረባቸው ሰዎች ናቸው። የህመም ምልክቶቹን ማወቅ እና ምልክቶቹ የታዩ እንደሆን ለሀኪም ማሳወቅ ያስፈልጋል። ይህ ህመም ሲኖር ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶች

  • አንገት አከባቢ ህመም
  • አንገት አከባቢ ሲዳስሱ ጠጣር ነገር (እጢ) መኖር
  • የድምጽ መለወጥ
  • ለመዋጥ ወይም ለመተንፈስ መቸገር
  • ሳል ናቸው።

የአይን ህመም:-  በአይነት ሁለት የስኳር በሽታ ምክንያት የአይን ህመም (Retinopathy) ሊባባስ ይችላል። ይህን መድሀኒት ሲወስዱ የአይን ምርመራ የቅርብ ክትትል እንዲያደርጉ ይመከራል።

የምግብ መንሸራሸር ችግር:- አይነት ሁለት የስኳር በሽታ ከሚያመጣው ህመም አንዱ የምግብ መንሸራሸር ችግር (gastroparesis) አንዱ ነው። ይህ ህመም ያጋጠማቸው ሰዎች ሰማግሉታይድ ከመውሰዳቸው በፊት ከሀኪማቸው ጋር ስለተሻለ አማራጭ ቢማከሩ ጥሩ ነው።

የጣፊያ ህመም:- ይህ መድሀኒት የጣፊያ ህመም (pancreatitis) ሊያባብስ ይችላል። ይህ የጎን ጉዳት በተለይ የሀሞት ጠጠር ያለባቸውና የአልኮል መጠጥ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ላይ ሊታይ ይችላል። የዚህ ህመም ምልክቶች ሀይለኛ የማያቋርጥ እና እስከጀርባ ድረስ የሚሰማ የሆድ ህመም ማቅለሽለሽ ማስታወክ እና ዘይት ያለበት የሚመስል ሰገራ ሊሆን ይችላል። ይህን መድሀኒት እየወሰዱ እንዲህ ያለ ህመም የሚሰማው ሰው ለሀኪሙ እንዲያሳውቅ ይመከራል።

የኩላሊት በሽታ:- በጥቂት ሰዎች ላይ ሰማግሉታይድ የኩላሊት በሽታን ሊያባብስ ይችላል። በዚህ መድሀኒት ምክንያት የኩላሊት ህመማቸው የተባባሰባቸው ሰዎች መጀመሪያ የማቅለሽለሽ ማስታወክና ተቅማጥ አጋጥሟቸዋል። እነዚህ የህመም ምልክቶች የሰውነት ውሃ ይዘት መቀነስ (dehydration) ሊያስከትሉ ይችላሉ። የሰውነት ውሃ ይዘት መቀነስ የኩላሊት በሽታን ሊያባብስ ስለሚችል የኩላሊት ህመም ያለበት ሰው እንዲህ ያሉ ህመም ምልክቶች ከታየበት ለሀኪም እንዲያሳውቅ ይመከራል።

የሰውነት መቆጣት (አደገኛ አለርጂ)፦ አንዳንድ ሰዎች ለዚህ መድሀኒት አደገኛ የሰውነት መቆጣት (አደገኛ አለርጂ) ሊኖራቸው ይችላል። አናፍላክሲስና (Anaphylaxis) አንጂዮኢዴማ (Angioedema) አጣዳፊ ህክምና የሚያስፈልጋቸው አለርጂ አይነቶች ናቸው። የህመም ምልክቶች ከታዩ ሀኪም ጋር መሄድ አስፈላጊ ነው። ዋና  ዋና ምልክቶች እነዚህን ያካትታል

  • ለመተንፈስ መቸገር
  • የፊት የምላስ የከንፈር ወይም የጉሮሮ ማበጥ
  • የቆዳ ሽፍታ እና ማሳከክ
  • የማዞር ስሜት
  • የልብ ትርታ መጨመር

የሀሞት ጠጠር፦ ይህን መድሀኒት የሚወስዱ ጥቂት ሰዎች የሀሞት ጠጠር አጋጥሟቸዋል። የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩ የዚህ ህመም ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ለሀኪም ማሳወቅ ተገቢ ነው።

  • በሆድ የላይኛውና የቀኝ ክፍል የሚሰማ ህመም
  • ትኩሳት
  • ማቅለሽለሽና ማስታወክ
  • የአይን ነጭ ክፍል ወደቢጫ መለወጥ

የደም ግሉኮስ ማነስ፦ ይህ መድሀኒት ብቻውን ሲወሰድ ዝቅተኛ የደም ግሉኮስ (hypoglycemia) አያመጣም ማለት ይቻላል። ነገር ግን ከሌሎች የስኳር በሽታ መድሀኒቶች  ጋር እንደተጨማሪ በሚወሰድበት ጊዜ የዝቅተኛ የደም ግሉኮስ (Hypoglycemia) ምልክቶችንና መወሰድ ያለበትን ጥንቃቄ ማወቅ ያስፈልጋል።

ሀይፓግላይስሚያ (Hypoglycemia)

የደም ግሉኮስ ሲለካ ከ70 በታች ሲሆን ወይም አንዳንድ የህመም ምልክቶች ሲታዩ የደም ግሉኮስ ማነስ (Hypoglycemia) ይባላል። እንደከፍተኛ የደም ግሉኮስ ሁሉ ይህ የደም ግሉኮስ በጣም ዝቅ ማለት ለጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል።

ይህን የጎን ጉዳት ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮች ውስጥ መድሀኒቱን ያለምግብ መውሰድ፣ በቂ ምግብ አለመመገብ፣ እና ሌሎች አንዳንድ መድሀኒቶች ናቸው። እንዲሁም ከ65 አመት በላይ እድሜ ያላቸው ሰዎች ለዚህ ጎን ጉዳት የበለጠ የተጋለጡ ናቸው። ምልክቶቹን ማወቅ እና ጥንቃቄ ማድረግ ጥሩ ነው።

ዋና ዋና የህመም ምልክቶች 

  • የረሀብ ስሜት
  • የመንቀጥቀጥ ስሜት
  • በላብ መጠመቅ
  • ብዥታ
  • የሰውነት መዛል
  • ያለተለመደ ግራ መጋባት (confusion)
  • ራስ ማዞር
  • የልብ በሀይል መምታት፣
  • እንዲሁም ከባሰ እራስን መሳት ናቸው።

እነዚህ ምልክቶች የተሰማው ሰው የሚከተሉትን ማድረግ አለበት

  1. ከተቻለ የደም ግሉኮስ መለካት
  2. ይህ ካልተቻለ ወይም ተለክቶ የደም ግልኮስ ከ70 በታች ከሆነ ስኳርነት ያለው ምግብ ወይም መጠጥ መውሰድ። ለምሳሌ የግሉኮስ ታብሌት፣ አንድ ማንኪያ ስኳር፣ ማር፣ ከረሜላ፣ ግማሽ ብርጭቆ የብርቱካን ጭማቂ ወይም አንድ ብርጭቆ ወተት መውሰድ ይቻላል።
  3. ከ15 ደቂቃ በሁዋላ የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ በድጋሚ መለካት።
  4. ተለክተው ከ70 በላይ ከሆነ ቀለል ያለ ምግብ መመገብ
  5. ተለክተው ከ70 በታች ከሆነ ከ 1 –3 ያሉትን የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ እስኪሆን ድረስ መደጋገም።
  6. የስኳር በሽታዎን ለሚከታተል ሀኪምዎ መንገር አይርሱ።

ለሰማግሉታይድ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ (FDA Blackbox Warning)

  • በቤተሰብ ወይም የታይሮይድ ካንሰር ወይም እጢ (thyroid tumor) ያለባቸው (የነበረባቸው) ሰዎች ይህ መድሀኒት መውሰድ የለባቸውም።
  • በቤተሰብ ወይም ራሳቸው የኢንዶክሪን ኒዮፕላዝያ ሲንድሮም (Multiple Endocrine Neoplasia Syndrome) ያለባቸው ሰዎች ይህ መድሀኒት መውሰድ የለባቸውም።

መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ

ራይበልሰስ
  • ይህ መድሀኒት እርጥበትና ሙቀት በሌለበት ህጻናት በማይደርሱበት ቦታ ይቀመጣል።
  • መድሀኒቱን በመጣበት ካርቶን ማስቀመጥ ጥሩ ነው።
ኦዘምፒክ
  • ያልተጀመረ ፔን ማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) ውስጥ ይቀመጣል። የበረዶ ቤት (freezer) ውስጥ መቀመጥ የለበትም። መድሀኒቱ በረዶ ከሰራ ይበላሻል። ስለዚህ ማቀዝቀዣው ውስጥ በረዶ ከሚሰራው ክፍል ርቆ መቀመጥ አለበት።
  • የተጀመረ ፔን ከማቀዝቀዣ ውጭ እርጥበት በሌለበት ህጻናት በማይደርሱበት ቦታ መቀመጥ ይችላል።
  • ከማቀዝቀዣ ውጭ የተቀመጠ ወይም የተጀመረ ፔን ለ 56 ቀን ሳይበላሽ ይቆያል።
  • የጸሀይ ብርሀን መድሀኒቱን ሊያበላሸው ይችላል። ስለዚህ ፔኑ ሁሌም መከደን እና የጸሀይ ብርሀን የማይደርስበት ቦታ መቀመጥ አለበት።

የኦዘምቢክ (ሰማግሉታይድ) ፔን አጠቃም

የሚያስፈልጉ ነገሮች

  • ኦዘምፒክ ፔን
  • የፔን መርፌ
  • አልኮል ስዋብ
  • የመርፌ መጣያ
ozembic Amharic
ስዕል 1 የኦዘምፒክ ፔን እና ክፍሎች
መሳሪያውን ማዘጋጀት ወይም አክቲቬት ማድረግ

አዲስ የሊክሲሰናታይድ ፔን ከጀመሩ በፊት መዘጋጀት (አክቲቬት መደረግ) አለበት ይህ የሚደረገው አዲስ ፔን ለመጀመሪያ ግዜ ሲጠቀሙ ብቻ ነው። አክትቬት ማድረግ ወይም መርፌውን ማዘጋጀት ለመጀመሪያ ግዜ የሚወሰደው የመደሀኒት መጠን ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው። የመጀመሪያው ቀን አክትቬት ከተደረገ በኋላ ለሚቀጥሉት 13 ቀኖች መደገም የለበትም። ፔኑን አክቲቬት ለማድረግ የሚከተሉትን ቅደም ተከተሎች ያንብቡ፦

ፔኑን ማዘጋጀት

አዲስ የኦዘምፒክ ፔን  ከመወሰዱ በፊት መዘጋጀት ወይም አክቲቬት መደረግ አለበት። አንድ ፔን አክቲቬት የሚደረገው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ፔኑን ለማዘጋጀት የሚከተሉትን ማድረግ ያስፈልጋል።

እጅ በውሀና በሳሙና መታጠብ

ፔኑን ከፍሪጅ ማውጣት ከዛም የፔኑን ክዳን  ከፍቶ በመድሀኒት ማሳያ መስኮት  በኩል የሚታየው መድሀኒት ንጹህ ጠጣር (ጓጓላ) ነገር የሌለው እንዲሁም እንድውሀ ቀለም የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ።

  • ፈሳሹ መልኩን ከቀየረ ወይም ውስጡ የሚታይ ጠጣር ነገር ካለው ይህንን ፔን መጠቀም አያስፈልግም።
መርፌ መግጠም
  1. ከመርፌው ጀርባ ላይ የሚገኘውን የሚላጥ የወረቀት መሸፈኛ  ማንሳት
  2. የመርፌውን የውጭ ክዳን በመያዝ መርፌውን ከፔኑ የመርፌ ማሰሪያ ጋር ማያያዝና እያዞሩ ማጥበቅ
  3. የመፌውን የውጭ ክዳን ጎትቶ ማውለቅ (ይህን የውጭ ክዳን ቅርብ ማስቀመጥ ያስፈልጋል)
  4. የመርፌውን የውስጥ ክዳን ጎትቶ ማውለቅ። ይህንን የውስጥ ክዳን መጣል ይቻላል። `
    • በዚህ ጊዜ የመርፌው ጫፍ ላይ ፈሳሽ ሊታይ ይችላል። ይህ ችግር የለውም።
Aldyxin patient education
ስዕል 2 የፔን መርፌ
መድሀኒቱ እንደሚፈስ ማረጋገጥ
  • የመድሀኒቱን መጠን መምረጫ ቀለበት በማዞር በመድሀኒት መጠን ጠቋሚ መስኮት ላይ ጥቁር ነጠብጣቦች እንደምታዩ ማረጋገጥ።
Ozempic Amharic
ስዕል 3 የመድሀኒንት መምረጫ ቀለበቱን ማዞር
  • መርፌው ወደላይ እንዲሆን አድርጎ ፔኑን ወደላይ ቀጥ አድርጎ መያዝየመድሀኒት መጠን ጠቋሚ መስኮቱ  ላይ “0” የሚል ቁጥር እስከሚታይ ድረስ የመጫኛ ቁልፉን  መጫን
  • በዚህን ጊዜ የመርፌው ጫፍ ላይ ቢያንስ አንድ ጠብታ ፈሳሽ እንደምታይ ማረጋገጥ
  • በመርፌው ጫፍ ላይ መድሀኒት ካልታየ ከ “ሐ” ስር የተጠቀሱትን እስከስድስት ጊዜ መደጋገም
  • ከስድስት ጊዜ ሙከራ በኋላ ጠብታ ፈሳሽ መርፌው ጫፍ ላይ ካልታየ መርፌውን ቀይሮ መሞከር
  • መድሀኒቱን ለመውሰድ ዝግጁ ከሆነ ከዚህ በታች የተጻፈውን ያንብቡ። ዝግጁ ካልሆኑ መርፌውን አውልቆ በተገቢ የመርፊው መጣያ ውስጥ መጣል። ፔኑን ከድነው ንጹህ እርጥበት ሙቀትና ልጆች የማይደርሱበት ቦታ ማስቀመጥ።
  • መርፊውን ተቀይሮ መድሀኒቱ በመርፊው ጫፍ ላይ የማይታይ ከሆነ ይህንን ፔን መጠቀም አያስፈልግም
Ozempic Amharic
ስዕል 4 ፔኑን ቀጥ አድርጎ መጫኛ ቁልፉን መጫን
የእለት ተእለት አጠቃቀም

እጅ በውሀና በሳሙና መታጠብ

ፔኑን ከፍሪጅ ማውጣት ከዛም የፔኑን ክዳን  ከፍቶ በመድሀኒት ማሳያ መስኮት  በኩል የሚታየው መድሀኒት ንጹህ ጠጣር (ጓጓላ) ነገር የሌለው እንዲሁም እንድውሀ ቀለም የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ።

  • ፈሳሹ መልኩን ከቀየረ ወይም ውስጡ የሚታይ ጠጣር ነገር ካለው ይህንን ፔን መጠቀም አያስፈልግም።
መርፌ መግጠም
  1. ከመርፌው ጀርባ ላይ የሚገኘውን የሚላጥ የወረቀት መሸፈኛ  ማንሳት
  2. የመርፌውን የውጭ ክዳን በመያዝ መርፌውን ከፔኑ የመርፌ ማሰሪያ ጋር ማያያዝና እያዞሩ ማጥበቅ
  3. የመፌውን የውጭ ክዳን ጎትቶ ማውለቅ (ይህን የውጭ ክዳን ቅርብ ማስቀመጥ ያስፈልጋል)
  4. የመርፌውን የውስጥ ክዳን ጎትቶ ማውለቅ። ይህንን የውስጥ ክዳን መጣል ይቻላል። `
    • በዚህ ጊዜ የመርፌው ጫፍ ላይ ፈሳሽ ሊታይ ይችላል። ይህ ችግር የለውም።
መድሀኒቱን መሙላት

የመድሀኒት መጠን ጠቋሚ መስኮት ላይ ሀኪም ያዘዘው የመድሀኒት መጠን እስከሚታይ ድረስ የመድሀኒቱን መጠን መምረጫ ቀለበት ማዞር።

    • የመድሀኒት መጠን መምረጫ ቀለበቱ በዞረ ቁጥር “ቀጭ” የሚል ድምጽ ይሰማል። ይህንን እንደምልክት መጠቀም ጥሩ አይደለም።
    • የመድሀኒት መምረጫ መስኮት “1” ቁጥር ከማሳየቱ በፊት መድሀኒት መጠን መምረጫ ቀለበቱ አልዞር ካለ በቂ መድሀኒት ፔኑ ውስጥ የለም ማለት ነው። ስለዚህ ሌላ ፔን መጠቀም ያስፈልጋል
መድሀኒቱን መወጋት

ኦዘምቢክ ወደቆዳ ስር የሚወጋ መድሀኒት ነው። ትክክለኛ የመወጊያ ቦታዎችን ለማወቅ የሚከተለውን ስእል 5 ላይ መመልከት ይቻላል።

  • ለመወጋት የተመረጠውን ቦታ በአልኮል ስዋብ ማጽዳት
  • መርፌውን ከመወጋት በፊት አልኮሉ መድረቁን ማረጋገጥ
Ozempic Amharic
ስዕል 5 ኦዘምቢክን ለመወጋት ተገቢ የሆኑ የሰውነት ክፍሎች

መርፌውን የተጸዳው ሰውነት ላይ መውጋት

    • የፔኑን የመድሀኒት መምረጫ መስኮት  እንዲታይ አድርጎ መያዝ ያስፈልጋል

የመድሀኒት መጠን መምረጫ መስኮቱ  ላይ “0” የሚል ቁጥር እስከሚታይ ድረስ የመጫኛ ቁልፉን ተጭኖ መቆየት

    • “ቀጭ” ወይም “ክሊክ” የሚል ድምጽ ሊሰማ ይችላል
    • መርፌው ሰውነት ውስጥ እንደተሰካና የመጫኛ ቁልፉን እንደተጫኑ እስከ ስድስት ቀስ እያሉ መቁጠር (ወይም ስድስት ሰከንድ መቆየት)
    • መርፊውን ቸኩሎ መንቀል በቂ የመድሀኒት መጠን እንዳያገኙ ያደርጋል።
    • ለስድስት ሰከንድ ያህል የመጫኛ ቁልፉን ተጭኖ ከተቆየ በኋላ የመድሀኒት መጠን መምረጫ መስኮት  ላይ “0” ካልታየ መርፌው ተደፍኖ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ከሆነ መርፌውን ቀይሮ እንደገና በ “ሠ” ስር ያሉትን መድገም ያስፈልጋል።
Ozempic Amharic
ስዕል 6 መድሀኒቱን ከወጉ በኋላ መጫኛ ቁልፉን ይዞ እስከስድስት ቀስ እያሉ መቁጠር
መርፊውን መንቀልና ማስወገድ
  • መርፌው ሲነቀል በመርፌው ጫፍ ላይ ጠብታ የመድሀኒት ፈሳሽ ሊታይ ይችላል። ይህ ምንም ችግር የለውም።
  • መርፌውን በጥንቃቄ ከፔኑ ላይ መፍታት
  • መርፊውን ህጻናት የማይደርሱበት ለዚሁ መጣያ ተብሎ በተዘጋጀ ክዳን ባለው የመጣያ እቃ ውስጥ ያስወግዱ።
  • ፔኑን በራሱ ክዳን መክደን መድሀኒቱን ከጸሀይ ብርሀን ይከላከለዋል። ስለዚህ ሁሌ የኦዘምፒክ ፔን ሲቀመጥ መርፌው ተነቅሎና በራሱ ክዳን ተከድኖ መሆን አለበት።

ማጣቀሻ

ቀን: 02/19/21

Disclaimer: All pictures and diagrams used in this post are not HIA’a property.

የሰማግሉታይድ ኩፓኖች

ይህ መድሀኒት ከሌሎች የስኳር በሽታ መድሀኒቶች ጋር ሲወዳደር ዋጋው በጣም ውድ ነው።

9.2/10
የአምራቹ ኩፓን

የኦዘምፒክና ራይበልሰስ (ሰማግሉታይድ) አምራች ለተጠቃሚዎች ቅናሽ ይሰጣል። ነገር ግን ማመልከቻ ማስገባትና መስፈርቶችን ማሟላት ያስፈልጋል።  ሁሉንም መስፈርት ለማየት የአምራቹን ድረገፅ ይጎብኙ።

ማውጫ