የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ ሊራግሉታይድ (Liraglutide)
ብራንድ ስም፦ ቪክቶዛ (Victoza) ሳክሴንዳ (Saxenda)
ምድብ፦ ጂኤልፒ 1 አይነት (GLP-1 Agonist)
ሊራግሉታይድ ለምን ይታዘዛል?
- በአይነት 2 ስኳር በሽታ ህመምተኞች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል
- በአይነት 2 ስኳር በሽታ ህመምተኞች ላይ አደገኛ የልብ እና የደም ስር በሽታዎችን ለመከላከል ይረዳል።የልብ እና የደም ስር በሽታ የልብ በሽታ (Heart attack) እና ስትሮክ (stroke)ን ያካትታል።
- ሳክሴንዳ (Saxenda)፦ ሰውነት ክብደታቸው በቢኤም አይ (BMI) ሲለካ ከ30 (kg/m2)በላይ ለሆኑ ወይም ቢኤም አይ ከ 27 (kg/m2) በላይ ሆኖ በውፍረት ምክንያት የሚመጣ በሽታ ላለባቸው ሰዎች ውፍረት ለመቀነስ ይረዳል።
ሊራግሉታይድ በምን መልኩ ይመረታል?
- ሊራግሉታይድ በቆዳ ስር የሚወጋ መርፌ ነው። የመድሀኒቱ እቃ ስም ፔን (ብእር ስለሚመስል) ይባላል።
- አንድ አንድ ፔን በውስጡ 3 ሚሊሊትር መድሀኒት ይይዛል።
- ሊራግሉታይድ በአንድ ጊዜ 6፣ 1.2 ወይም 1.8 ሚሊግራም እንዲሰጥ ተደርጎ ይመረታል።
- አንድ ፔን ለብዙ ጊዜ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ለ30 ቀን ያገለግላል።
ሊራግሉታይድ እንዴት ነው የሚሰራው?
ሊራግሉታይድ በሰውነት ውስጥ የኢንሱሊንን መጠን በመጨመር እና የግሉካንን መጠን በመቀነስ የደም ግሉኮስን ያስተካክላል።
ሊራግሉታይድ በተፈጥሮ ሰውነት ውስጥ የሚገኘውን ጂኤልፒ 1 እንዲመስል ተደርጎ የተሰራ መድሀኒት ነው። ጂኤልፒ 1 በአንጀት ከሚገኙ ኢንክሪቲን ከሚባሉ ሆርሞኖች መካከል አንዱ ሲሆን የሚጠቅመው ምግብ ከተበላ ብኋላ ከፍ ያለ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል ነው። ጂኤልፒ 1 የሚሰራው በሰውነት ውስጥ ከፍተኛ የግሉኮስ መጠን ሲኖር ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ ጂኤልፒ 1 ቢኖር እንኳን የደም ግልኮስን ዝቅ አያደርግም።
ጂኤልፒ 1 የደም ግሉኮስን የሚቆጣጠረው አንድም ጣፊያ የኢንሱሊን ምርቱን እንዲጨምር በማድረግ ደግሞም የግሉካጎን ምርቱን እንዲቀንስ በማድረግ ነው። የኢንሱሊን መጠን መጨመር በደም ያለውን የግሉኮስ መጠን ይቀንሳል። የግሉካጎን መጠን መቀነስ ደግሞ በግላይኮጅን መልክ ተከማችቶ የሚቀመጠውን ግሉኮስ ወደደም ዝውውር እንዳይገባ ያደርገዋል። ምግብ ከተበላ ከጥቂት ሰአት በኋላ ጂኤልፒ 1 እና ሌሎች ኢንክሪቲኖች በዲፒፒ 4 ኢንዛይም ይሰባበራሉ። በዲፒፒ 4 የተሰባበሩ ኢንክሪቲኖች (ጂኤልፒ-1 ን ጨምሮ) የደም ግሉኮስን ማስተካከል አይችሉም።
ሊራግሉታይድ የሚሰራው በተፈጥሮ ከሚገኘው ጂኤልፒ 1 ጋር በተመሳሳይ መንገድ ነው። ነገር ግን በተፈጥሮ እንደሚገኘው ጂኤልፒ 1 በዲፒፒ 4 አይሰባበርም። ስለዚህ በሰውነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቆየት እና የደም ግሉኮስን ማስተካከል ይችላል።
በተጨማሪ ጂኤልፒ 1 የምግብ መንሸራሸርን ያዘገያል። ይህም የሆድ መሙላት ወይም የመጥገብ ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል። በዚህ ምክንያት በምግብ መልኩ ወደሰውነት የሚገባው የግሉኮስን መጠን ይቀንሳል።
የሊራግሉታይድ አወሳሰድ
- የሀኪምዎን ትእዛዝ ይከተሉ።
- የሚታዘዘው የመድሀኒት መጠን በሀኪም ውሳኔ መሰረት እንደታካሚው ይለያያል።
- ብዙ ጊዜ በቀን አንዴ ቆዳ ስር ይወጋል።
- የሚወጋበት ቦታ ሆድ ክንድ ወይም ታፋ ላይ ብቻ መሆን አለበት።
- ይህ መድሀኒት ከሌላ የሚወጉ መድሀኒቶች ጋር መቀላቀል የለበትም።
- የኢንሱሊን እና ሊራግሉታይድ አጠገብ ለአጠገብ መወጋት የለበትም።
(የሊራግሉታይድን ፔን አጠቃቀም በዝርዝር ለማየት ወደጽሁፉ መጨረሻ “የሊራግሉታይድ ፔን አጠቃቀም” የሚለውን ርእስ ይመልከቱ)
መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?
በሶስት ቀን ውስጥ ካስታወሱ በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ጊዜ የተለመደውን መጠን ይውሰዱ። የረሱትን ጨምረው ለመውሰድ አይሞክሩ። መድሀኒቱን ከወሰዱ 3 ቀን ካለፈ ምን ማድረግ እንዳለብዎ ለማወቅ ሀኪምዎን ወይም ፋርማሲስት ያማክሩ።
የሊክሲሰናታይድ የጎን ጉዳት (Side-effect)
ይህን መድሀኒት የሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች ላይ እነዚህ የህመም ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ
- ማቅለሽለሽ
- ማስታወክ
- ተቅማጥ
- የሆድ ድርቀት
- የምግብ ፍላጎት መቀነስ
- የምግብ አለመንሸራሸርና አለመፈጨት ችግር
- መድሀኒት የተወጋበት ቦታ ህመም
- የልብ ምት መጨመር
- የራስምታት
ይህ ብዙ ጊዜ መድሀኒቱ ሲጀመር አከባቢ የሚሰማ ህመም ነው። መድሀኒቱ ከሰውነት ጋር ሲላመድ ይተዋል። ካልተወ ወይም ከአቅም በላይ ከሆነ ግን ለሀኪም ያማክሩ።
ለዚህ መድሃኒት የሃኪም ክትትል ያስፈልገኛል?
የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሀኪም ክትትል ያስፈልጋቸዋል። ይህም የሚደረገው
- የታዘዘላቸው መድሀኒት የደም ግሉኮሳቸውን በመቆጣጠር ያመጣውን ውጤት ለማወቅ
- በመድሀኒቱ ምክንያት የሚመጣ የጎን ጉዳት ካለ ለማወቅ
- በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጣ ሌላ ህመም (ለምሳሌ የኩላሊት በሽታ) ካለ በጊዜ ለማወቅ እና የሚያስፈልገውን ህክምና ለማድረግ ነው።
ሊራግሉታይድን ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ምንድነው?
ይህ መድሀኒት የሚሰራው ሀኪም ባዘዘው መሰረት በየእለቱ ሲወሰድ ነው።
ከመድሀኒቱ በተጨማሪ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግና አመጋገብ ማስተካከል የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋፆ አለው።
ይህ መድሀኒት የደም ግሉኮስን ያስተካክላል እንጂ የስኳር በሽታን አይፈውስም። የስኳር በሽታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ህመም ነው። የህክምናው አላማ የደም ግሉኮስን በመቀነስ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ ኩላሊት እና አይን) ላይ የሚያደርሰውን በሽታ መከላከል ነው። የደም ግሉኮስ ሲቀንስ ይህን መድሀኒት መውሰድ ማቆም የደም ግሉኮስ ተመልሶ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ የደም ግሉኮስ ቢስተካከል ወይም ጤንነት ቢሰማ እንኳን ይህን መድሀኒት ያለሀኪም ትእዛዝ ማቋረጥ አይመከርም።
ሊራግሉታይድ የማይታዘዝላቸው ሰዎች (Contraindication and limitations)
- በቤተሰብ ወይም ራሳቸው የታይሮይድ እጢ (thyroid tumor) ያለባቸው ሰዎች
- ከዚህ በፊት ይህን መድሀኒት ወስደው አደገኛ አለርጂ ያጋጠማቸው ሰዎች
- አይነት አንድ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች እንዲሁም
- ከስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ ኪቶአሲዶሲስ (diabetic ketoacidosis) ያጋጠማቸው ሰዎች።
የመድሀኒቱ መስተጋብር (Drug Interaction)
አልኮል፦ እንደብዙ መድሀኒቶች ሁሉ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ አልኮል መጠጥ መጠጣት አይመከርም።
እርጉዝ ሴቶች፦ ለእርጉዝ ሴቶች ከሊራግሉታይድ የተሻለ መድሀኒት ሊኖር ይችላል። በእርግዝና ግዜ የስኳር በሽታን መቆጣጠር ለእናትም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት ማርገዟን ስታውቅ መድሀኒቱን ላዘዘላት ሀኪም እንድታሳውቅ ይመከራል።
የሚያጠቡ ሴቶች፦ የሚያጠቡ ሴቶች ይህን መድሀኒት ሲወስዱ ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ ሀኪማቸውን ያማክሩ።
ምግቦች፦ ይህን መድሀኒት ሲወስዱ ጣፋጭ የሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ ካርቦሀይድሬት (carbohydrate) ያላቸውን ምግቦች (ለምሳሌ ዳቦ፣ ፓስታ፣ ጣፋጭ ፍራፍሬዎች) ይቀንሱ። ለስኳር በሽታ ተስማሚ የሆነ የአመጋገብ መከተል ለመድሀኒቱ መስራት እና ለአጠቃላይ ጤንነት ጥሩ ነው።
ሌሎች ጥንቃቄዎች
የጎን ጉዳቶችን ለመቀነስና ሰውነትን ለማላመድ ሀኪም በትንሽ የመድሀኒት መጠን ጀምሮ እየጨመረ ሊሄድ ይችላል። ብዙ ሰዎች 0.6 ሚሊግራም በቀን አንድ ግዜ ለአንድ ሳምንት ይታዘዝላቸውና ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ 1.2 ሚሊግራም በቀን አንድ ጊዜ እንዲወስዱ ይደረጋል። ሀኪም በሚያደርገው ምርመራ ይህንን መጠን እየጨመረ ሊሄድ ይችላል።
የምግብ መንሸራሸር ችግር፦ አይነት ሁለት የስኳር በሽታ ከሚያመጣው ህመም አንዱ የምግብ መንሸራሸር ችግር (gastroparesis) አንዱ ነው። ይህ ህመም ያጋጠማቸው ሰዎች ሊራግሉታይድ (Victoza) ከመውሰዳቸው በፊት ከሀኪማቸው ጋር ስለተሻለ አማራጭ ቢማከሩ ጥሩ ነው።
የታይሮይድ እጢ:- ይህንን መድሀኒት የወሰዱ ጥቂት ሰዎች የታይሮይድ እጢ አጋጥሟቸዋል። ይህ የጎን ጉዳት ያጋጠማቸው ሰዎች በቤተሰብ ወይም ራሳቸው የታይሮይድ እጢ የነበረባቸው ሰዎች ናቸው። የህመም ምልክቶቹን ማወቅ እና ምልክቶቹ የታዩ እንደሆን ለሀኪም ማሳወቅ ያስፈልጋል። የዚህ ህመም ምልክቶች
- አንገት አከባቢ ህመም
- አንገት አከባቢ ሲዳስሱ ጠጣር ነገር (እጢ) መኖር
- የድምጽ መለወጥ
- ምግብ/መጠጥ ሲውጡ ማመም ወይም ለመዋጥ መቸገር
- የትንፋሽ ማጠር ናቸው።
የጣፊያ ህመም:- ይህ መድሀኒት የጣፊያ ህመም (pancreatitis) ሊያባብስ ይችላል። ይህ የጎን ጉዳት በተለይ የሀሞት ጠጠር ያለባቸውና የአልኮል መጠጥ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ላይ ሊታይ ይችላል። የዚህ ህመም ምልክቶች ሀይለኛ የማያቋርጥ እና እስከጀርባ ድረስ የሚሰማ የሆድ ህመም ማቅለሽለሽ ማስታወክ እና ዘይት ያለበት የሚመስል ሰገራ ሊሆን ይችላል። ይህን መድሀኒት እየወሰዱ እንዲህ ያለ ህመም የሚሰማው ሰው ለሀኪሙ እንዲያሳውቅ ይመከራል።
የኩላሊት በሽታ:- በጥቂት ሰዎች ላይ ሊራግሉታይድ የኩላሊት በሽታን ሊያባብስ ይችላል። በዚህ መድሀኒት ምክንያት የኩላሊት ህመማቸው የተባባሰባቸው ሰዎች መጀመሪያ የማቅለሽለሽ፣ የማስታወክና የተቅማጥ አጋጥሟቸዋል። እነዚህ የህመም ምልክቶች የሰውነት ውሃ ይዘት መቀነስ (dehydration) ሊያስከትሉ ይችላሉ። የሰውነት ውሃ ይዘት መቀነስ የኩላሊት በሽታን ሊያባብስ ስለሚችል የኩላሊት ህመም ያለበት ሰው እንዲህ ያሉ ህመም ምልክቶች ከታየበት ለሀኪም እንዲያሳውቅ ይመከራል።
የሀሞት ከረጢት በሽታ:- ይህን መድሀኒት የሚወስዱ ጥቂት ሰዎች የሀሞት ከረጢት በሽታ አጋጥሟቸዋል። የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩ የዚህ ህመም ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ለሀኪም ማሳወቅ ተገቢ ነው።
- በሆድ የላይኛውና የቀኝ ክፍል የሚሰማ ህመም
- ትኩሳት
- ማቅለሽለሽና ማስታወክ
- የአይን ነጭ ክፍል ወደቢጫ መለወጥ
የሰውነት መቆጣት (አደገኛ አለርጂ)፦ አንዳንድ ሰዎች ለዚህ መድሀኒት አደገኛ የሰውነት መቆጣት (አደገኛ አለርጂ) ሊኖራቸው ይችላል። አናፍላክሲስና (Anaphylaxis) አንጂዮኢዴማ (Angioedema) አጣዳፊ ህክምና የሚያስፈልጋቸው አለርጂ አይነቶች ናቸው። የህመም ምልክቶች ከታዩ ሀኪም ጋር መሄድ አስፈላጊ ነው። ዋና ዋና ምልክቶች እነዚህን ያካትታል
- ለመተንፈስ መቸገር
- የፊት የምላስ የከንፈር ወይም የጉሮሮ ማበጥ
- የቆዳ ሽፍታ እና ማሳከክ
- የማዞር ስሜት
- የልብ ትርታ መጨመር
የደም ግሉኮስ ማነስ፦ ይህ መድሀኒት ብቻውን ሲወሰድ የደም ግሉኮስን ከሚፈለገው በታች ዝቅ አያደርግም። ነገር ግን ከሌሎች የስኳር በሽታ መድሀኒቶች ጋር እንደተጨማሪ ሊወሰድ ይችላል። በዚህ ግዜ የዝቅተኛ የደም ግሉኮስ (Hypoglycemia) ምልክቶችንና መወሰድ ያለበትን ጥንቃቄ ማወቅ ያስፈልጋል።
ሀይፓግላይስሚያ (Hypoglycemia)
የደም ግሉኮስ ሲለካ ከ70 በታች ሲሆን ወይም አንዳንድ የህመም ምልክቶች ሲታዩ የደም ግሉኮስ ማነስ (Hypoglycemia) ይባላል። እንደከፍተኛ የደም ግሉኮስ ሁሉ ይህ የደም ግሉኮስ በጣም ዝቅ ማለት ለጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል።
ይህን የጎን ጉዳት ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮች ውስጥ መድሀኒቱን ያለምግብ መውሰድ፣ በቂ ምግብ አለመመገብ፣ እና ሌሎች አንዳንድ መድሀኒቶች ናቸው። እንዲሁም ከ65 አመት በላይ እድሜ ያላቸው ሰዎች ለዚህ ጎን ጉዳት የበለጠ የተጋለጡ ናቸው። ምልክቶቹን ማወቅ እና ጥንቃቄ ማድረግ ጥሩ ነው።
ዋና ዋና የህመም ምልክቶች
- የረሀብ ስሜት
- የመንቀጥቀጥ ስሜት
- በላብ መጠመቅ
- ብዥታ
- የሰውነት መዛል
- ያለተለመደ ግራ መጋባት (confusion)
- ራስ ማዞር
- የልብ በሀይል መምታት፣
- እንዲሁም ከባሰ እራስን መሳት ናቸው።
እነዚህ ምልክቶች የተሰማው ሰው የሚከተሉትን ማድረግ አለበት
- ከተቻለ የደም ግሉኮስ መለካት
- ይህ ካልተቻለ ወይም ተለክቶ የደም ግልኮስ ከ70 በታች ከሆነ ስኳርነት ያለው ምግብ ወይም መጠጥ መውሰድ። ለምሳሌ የግሉኮስ ታብሌት፣ አንድ ማንኪያ ስኳር፣ ማር፣ ከረሜላ፣ ግማሽ ብርጭቆ የብርቱካን ጭማቂ ወይም አንድ ብርጭቆ ወተት መውሰድ ይቻላል።
- ከ15 ደቂቃ በሁዋላ የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ በድጋሚ መለካት።
- ተለክተው ከ70 በላይ ከሆነ ቀለል ያለ ምግብ መመገብ
- ተለክተው ከ70 በታች ከሆነ ከ 1 –3 ያሉትን የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ እስኪሆን ድረስ መደጋገም።
- የስኳር በሽታዎን ለሚከታተል ሀኪምዎ መንገር አይርሱ።
ጥብቅ ማስጠንቀቂያ (FDA Blackbox Warning)
- በቤተሰብ ወይም የታይሮይድ ካንሰር ወይም እጢ (thyroid tumor) ያለባቸው (የነበረባቸው) ሰዎች ይህ መድሀኒት አይታዘዝላቸውም።
- በቤተሰብ ወይም ራሳቸው የኢንዶክሪን ኒዮፕላዝማ (Multiple Endocrine Neoplasia Syndrome) ያለባቸው ሰዎች ይህ መድሀኒት አይታዘዝላቸውም።
መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ
- ያልተጀመረ መርፌ ማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) ውስጥ ይቀመጣል። የበረዶ ቤት (freezer) ውስጥ መቀመጥ የለበትም። መድሀኒቱ በረዶ ከሰራ ይበላሻል። ስለዚህ ማቀዝቀዣው ውስጥ በረዶ ከሚሰራው ክፍል ርቆ መቀመጥ አለበት።
- የተጀመረ መርፌ ማቀዝቀዣ ውስጥ ወይም ውጭ መቀመጥ ይችላል።
- መድሀኒት የሚቀመጥበት ቦታ እርጥበት የሌለበት ህጻናት የማይደርሱበት ቦታ ነው።
- አንድ መርፌ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ለሰላሳ ቀን መጠቀም ይቻላል። ከሰላሳ ቀን በኋላ ከአገልግሎት ውጭ ይሆናል።
የሊራግሉታይድ (የቪክቶዛ) ፔን አጠቃቀም
ይህን መድሀኒት ለመውሰድ ለብቻው የሚሸጥ የፔን መርፌ ያስፈልጋል።
- አንድ የፔን መርፌ ለአንድ ግዜ ብቻ መጠቀም ጥሩ ነው። መርፌ ደጋግሞ መጠቀም ለኢንፌክሽን ሊያጋልጥ ይችላል። በተጨማሪ መርፌው ሊደፈን እና መድሀኒቱ እንዳይወርድ ሊያደርገው ይችላል።
- የፔን መርፌ ሲገዛ ለምጠቀሙበት ፔን የሚሆን መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የትኛው የፔን መርፌ እንደሚሆን ከሀኪምዎ ወይም ከፋርማሲስት መጠየቅ ይችላሉ።
- መርፌና ፔን ከሌላ ሰው ጋር መጋራት በሽታ ሊያስተላልፍ ስለሚችል ፔንም ሆነ መርፌ ከሌላ ሰው ጋር መጋራት ጥሩ አይደለም።
ሀ
መሳሪያውን መፈተሽ
አዲስ የሊራግሉታይድ (ቪክቶዛ) ፔን ከፍሪጅ ከማውጣት በፊት እጅ በውሀ እና በሳሙና መታጠብ
የፔኑን ክዳን መክፈት እና በካርትሌጁ ውስጥ እንደውሀ ቀለም የሌለው ንጹህና ምንም አይነት ጠጣር ነገር የሌለው ፈሳሽ እንዳለው ማረጋገጥ።
ረበር ስቶፐሩን በአልኮል ስዋብ መወልወል
ለ
መርፌ መግጠም
- ከመርፌው ላይ የሚላጠውን የወረቀት ክዳን ማንሳት
- የመርፌውን የውጭ ክዳን በመያዝ መርፌውን ከፔኑ የመርፌ ማሰሪያ ጋር ማያያዝ እና እያዞሩ ማጥበቅ
- የመፌውን የውጭ ክዳን ጎትቶ ማውለቅ (ይህን የውጭ ክዳን ቅርብ ማስቀመጥ ያስፈልጋል)
- የመርፌውን የውስጥ ክዳን ጎትቶ ማውለቅ። ይህንን የውስጥ ክዳን መጣል ይቻላል። ይህን ግዜ ትንሽ እርጥበት ከመርፌው ጫፍ ላይ ሊወጣ ይችላል።
ሐ
መጫኛ ቁልፉን (1.7) መሳብየመድሀኒቱን ማፍሰስ
ይህ አዲስ ፔን ሲጀመር ብቻ የሚደረግ ነው። ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ ይህንን ክፍል መዝለል ያስፈልጋል።
የመድሀኒቱን መሙያ በማዞር መቁጠሪያው የመድሀኒት ማፍሰሻ ምልክት ላይ እንዲሆን ማድረግ
በአንድ እጅ የፔኑን መርፌ ወደላይ አድርጎ መያዝ
በሌላ እጅ ካርትሌጁን በጣት መታ መታ ማድረግ
መርፌው ወደላይ እንደሆነ ፔኑን በመያዝ የመድሀኒት መጠን መቁጠሪያው ዜሮ (0) እስከሚያነብ ድረስ የፔን መጫኛ ቁልፍን መጫን።
የመርፌው ጫፍ ላይ አንድ ጠብታ ፈሳሽ እስከሚወጣ ድረስ መድሀኒቱን ማፍሰስ የሚለው ስር ያለውን መደጋገም። ስድስት ግዜ ተሞክሮ አሁንም መድሀኒቱ የማይወጣ ከሆነ ለፋርማሲስት ወይም ለሀኪም ማማከር።
መድሀኒቱ ከወጣ በሀኪም የታዘዘውን የመድሀኒት መጠን ለመወጋት ወደ “መ” መቀጠል
መ
የመድሀኒቱን መጠን መሙላት
የመድሀኒቱን መሙያ በማዞር ሀኪም ያዘዘውን የመድሀኒት መጠን መሙላት። ይህ 0.6፣ 1.2 ወይም 1.8 ሚሊግራም ሊሆን ይችላል።
እያንዳንዱን የመድሀኒት መጠን ባለፈ ቁጥር “ክሊክ” የሚል ድምጽ ይሰማል። ነገር ግን ይህንን መተማመን ጥሩ አይደለም። ሁሌም ምን ያህል የመድሀኒት መጠን እንደተሞላ ለማወቅ የመድሀኒት መጠን መቁጠሪያ መስኮት ውስጥ ያለውን ቁጥር ማንበብ ያስፈልጋል።
የመድሀኒቱን መጠን ካለፉት ማዞርያውን ወደኋላ በማዞር ወደሚፈልጉት የመድሀኒት መጠን መመለስ ይቻላል።
ሠ
መድሀኒቱን ለመውሰድ
ይህን መድሀኒት ሆድ፣ ታፋ ወይም ክንድ ላይ መውጋት ይቻላል። ደምስር አከባቢ ወይም ጡንቻ ላይ መውጋት ትክክል አይደለም።
የተሞላውን የሊራግሉታይድ ፔን ቆዳ ላይ መሰካት። በአንድ እጅ ቆዳን ቆንጥጦ መያዝ ይቻላል። የመድሀኒቱን መቁጠሪያ መስኮት እንዲታይ ማድረግ ያስፈልጋል።
የመድሀኒቱ መቁጠሪያ መስኮት ላይ የሚታየው ቁጥር (”0”) ከመጠቆሚያው ጋር ትይዩ እስከሚሆን ድረስ የመድሀኒቱን መጫኛ ቁልፍ መጫን።
ቢያንስ ለ6 ሰከንድ ድረስ መርፌውን ቆዳው ውስጥ እንዳለ የመድሀኒቱን መጫኛ ቁልፍ እንደተጫኑ መቆየት። ይህ መድሀኒቱ ሙሉ በሙሉ እንደተወጋ ለማረጋገጥ ያገለግላል።
የሚወጉበትን ቦታ በየእለቱ መለዋወጥ ያስፈልጋል። ሆድ ላይ ሲወጉ አንድ ቀን ከእንብርት በስተግራ ከተወጋ በሚቀጥለው በስተቀኝ በኩል፣ በሚቀጥለው ቀን ከንብርት በላይ እያደረጉ ማዘዋወር ይቻላል። ነገር ግን የሚወጉበት ቦታ አጠገብ ላጠገብ መሆን የለበትም።
ረ
መርፌውን ከተወጉ በኋላ
መርፌው ሲነቀል ጠብታ ፈሳሽ ሊኖር ይችላል። ይህ ምንም ችግር የለውም።
መርፌው ሲነቀል ቆዳ ላይ ደም ከታየ በጣት መጫን ይቻላል። ነገር ግን ማሸት ትክክል አይደለም።
ሰ
መርፌውን ማስወገድ
- መርፌውን ከፔኑ ላይ ከመፍታት በፊት በመርፌው የውጭ ክዳን መክደን
- መርፌውን በማዞር ከፔኑ ላይ መፍታት
- አንድ መርፌ ከአንድ ግዜ በላይ መጠቀም ትክክል አይደለም
- መርፌውን ቢቻል ለዚሁ አገልግሎት የተዘጋጀ የመርፌ መጣያ ውስጥ መጣል። ይህ ካልተቻለ ግን ሌላ ሰው እንዳይወጋና ህጻናት የማይደርሱበት መጣያ ውስጥ መጣል ያስፈልጋል። ለመርፌ መጣያ ክዳን ባለው ጠንካራ ፕላሲክ ወይም ቆርቆሮ ማዘጋጀት ይቻላል።
የፔን ንጽህና እና ሌሎች ጥንቃቄዎች
- መድሀኒት ከተወሰደ በኋላ የሊራግሉታይድ ፔን ተከድኖ መቀመጥ አለበት። ከመርፌው ጋር እንደተያያዘ መቀመጥ የለበትም።
- የመድሀኒቱን ፔን ለመሙላት ወይም ለመፈታት መሞከር መድሀኒቱን ያበላሸዋል።
- የመድሀኒቱ ፔን እርጥበት የሌለበት ንጹህ ቦታ ማስቀመጥ ይቻላል።
- የመድሀኒቱን ፔን ማጽዳት ካስፈለገ በለዛዛ ጨርቅ ውጩን መወልወል ይቻላል።
- አንድ የመድሀኒት ፔን ከተጀመረ ወይም ከፍሪጅ ወቶ ከቆየ በኋላ የሚያገለግለው ለ30 ቀን ብቻ ነው።
ማጣቀሻ
- Brunton, Laurence L., et al. Goodman & Gilman’s: the Pharmacological Basis of Therapeutics. McGraw Hill Medical, 2018.
- “DailyMed – VICTOZA- Liraglutide Injection.” U.S. National Library of Medicine, National Institutes of Health, dailymed.nlm.nih.gov/dailymed/lookup.cfm?setid=5a9ef4ea-c76a-4d34-a604-27c5b505f5a4#i4i_dosage_admin_id_7b31fa3a-1f64-4c9e-8c27-4f4f6133f24e.
- “Diabetes Mellitus.” Pharmacotherapy Handbook, by Barbara G. Wells et al., McGraw-Hill Education, 2017, pp. 161–175.
- SAXENDA (liraglutide [rDNA origin] injection), solution for subcutaneous use. [package insert]. 2880 Bagsvaerd, Denmark: Novo Nordisk Inc.; 2020.
- VICTOZA®(liraglutide) injection, for subcutaneous use. [package insert]. 2880 Bagsvaerd, Denmark: Novo Nordisk Inc.; 2020.
ቀን: 02/04/21
Disclaimer: All pictures and diagrams used in this post do not belong to HIA.
የሊራግሉታይድ ኩፓኖች
ይህ መድሀኒት ከሌሎች የስኳር በሽታ መድሀኒቶች ጋር ሲወዳደር ዋጋው በጣም ውድ ነው።
የጉድ አር ኤክስ ኩፓን (GoodRx Coupon)
ጉድ አር ኤክስ ድረገጽ ላይ የመድሀኒቱን ስም ምን ያህል ሚሊግራም እንደሆነ እና የምን ያህል ፔን ወይም ካርቶን እንደሚፈለግ ካስገቡ በኋላ ቅናሽ የምያገኙበትን ካርድ ፕሪንት እንዲያደርጉ ይጠይቃል። ይህንን ካርድ ወደፋርማሲ ይዘው ይሂዱ። ጉድ አር ኤክስ እና ሌሎች ዲስካውንት ካርዶች ከመንግስት ኢንሹራንስ ጋር አይሰሩም።
የአምራቹ ኩፓን
የቪክቶዛ (ሊራግሉታይድ) አምራች ለተጠቃሚዎች ቅናሽ ይሰጣል። ነገር ግን ማመልከቻ ማስገባትና መስፈርቶችን ማሟላት ያስፈልጋል። ሁሉንም መስፈርት ለማየት የአምራቹን ድረገፅ ይጎብኙ።