Amharic Health Information

ግልፕዛይድ (Glipizide)

የመድሃኒት ስም ጀነሪክ፦ ግልፕዛይድ 

ምድብ፦ ሰልፎንይልዩርያ (Sulfonylurea)

ብራንድ ስም ግሉኮትሮል (Glucotrol, Glucotrol XL)

ግልፕዛይድ ለምን ይወሰዳል?

ግልፕዛይድ  በአይነት ሁለት ስኳር በሽታ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የደም ግሉኮስን ለማስተካከል ይረዳል።

ግልፕዛይድ እንዴት ነው የሚሰራው?

አይነት ሁለት የስኳር በሽታ ያለበት ሰው ኢንሱሊን የሚያመርተው የጣፍያ ህዋሶቹ (beta cells of pancreatic islet) ይደክማሉ። እነዚህ ህዋሶች ኢንሱሊን የማምረት አቅማቸው ዝቅተኛ ይሆናል። ኢንሱሊን ከሌለ በደም ውስጥ ያለው ግሉኮስ ወደሚያስፈልገው የሰውነት ክፍል መሄድ አይችልም። በዚህ ምክንያት በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን እየተጠራቀመ እና እየጨመረ ይሄዳል።

ግልፕዛይድ እነዚህን የተዳከሙ እንዲሁም የተቀሩትን ጤናማ የጣፊያ ህዋሶች የተሻለ መጠን ያለው ኢንሱሊን እንዲያመርቱ ያደርጋቸዋል። ይህ ኢንሱሊን በደም ውስጥ ያለው ግሉኮስ ወደሚያስፈልገው የሰውነት ክፍል ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የደም ግሉኮስ መጠንን እንዲቀንስ ያደርገዋል። 

ግልፕዛይድ በምን መልኩ ይመረታል?

በክኒን መልኩ ተመርቶ ገበያ ላይ ይቀርባል። ብዙ ጊዜ በ 2.5, በ5 እና በ10 ሚሊ ግራም (mg) መጠን ይመጣል። በተጨማሪ ግሉኮትሮል በሰውነት ውስጥ ቀስ ብሎ የሚሰራ ወይም ኤክስቴንድድ ሪሊዝ (extended-release) እንዲሆን ተደርጎ ይመረታል።

ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ምንድነው?

ይህ መድሀኒት የሚሰራው ሀኪም ባዘዘው መሰረት በየእለቱ ሲወሰድ ነው።

ከመድሀኒቱ በተጨማሪ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እና አመጋገብ ማስተካከል የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋፆ አለው።

ይህ መድሀኒት የደም ግሉኮስን ያስተካክላል እንጂ የስኳር በሽታን አይፈውስም። የስኳር በሽታ ለረጅም ግዜ የሚቆይ ህመም ነው። የህክምናው አላማ የደም ግሉኮስን በመቀነስ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ ኩላሊት እና አይን) ላይ የሚያደርሰውን በሽታ መከላከል ነው። የደም ግሉኮስ ሲቀንስ ይህን መድሀኒት መውሰድ ማቆም የደም ግሉኮስ ተመልሶ እንዲጨምር ሊያደርገው ይችላል። ስለዚህ የደም ግሉኮስ ቢስተካከል ወይም ጤንነት ቢሰማ እንኳን ይህን መድሀኒት ያለሀኪም ምክር ማቆም ትክክል አይደለም።

የመድሀኒት ግብብሮሽ

መድሀኒቶች፦  አዞል(Azole) የሚባሉ የመድሀኒት ምድብ ውስጥ የሚመደቡ መድሀኒቶች ለምሳሌ ዳይፍሉካን(Diflucan/fluconazole) ከዚህ መድሀኒት ጋር ሲወሰዱ የደም ግሉኮስን በሀይል ሊቀንስ ይችላሉ። ሌሎች መድሀኒቶችም እንዲህ አይነት ባህሪይ ሊኖራቸው ይችላል። ከነዚህም መካከል ያለሀኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ የህመም ማስታገሻዎች አድቪል (Advil) እና አሊቭ (Aleve) ይገኙበታል። ግልፕዛይድን እየወሰዱ አዲስ መድሀኒት ሲጀምሩ ሀኪምን ወይም ፋርማሲስት በማማከር ለጎን ጉዳት (side effect) እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ ያድርጉ።

አልኮል፦ እንደብዙ መድሀኒቶች ሁሉ ይህ መድሀኒት ከአልኮል ጋር አይስማማም።

እርጉዝ ሴቶች፦ ይህ መድሀኒት በእርግዝና ግዜ ከእናት ወደጽንስ ሊተላለፍ ይችላል። በእርግዝና ጊዜ የስኳር በሽታን መቆጣጠር ለእናትም ሆነ ለጽንስ ጤንነት አስፈላጊ ነው። ይህን መድሀኒት የምትወስድ ሴት መጸነሷን ስታውቅ መድሀኒቱን ላዘዘላት ሀኪም እንድታሳውቅ ይመከራል።

የሚያጠቡ ሴቶች፦ ግልፕዛይድ የሚወስዱ ሁለት ሴቶች የጡት ወተት ላይ በተደረገ ምርመራ መድሀኒቱ አልተገኘም። ነገር ግን ይህን የሚያረጋግጥ ሰፊ ጥናት የለም። ማድረግ ስላለብዎት ጥንቃቄ ሀኪምዎን ያማክሩ።

ይህ መድሀኒት የማይታዘዝላቸው ሰዎች

  1. ከዚህ በፊት ይህን መድሀኒት ወስደው አደገኛ አለርጂ ያጋጠማቸው ሰዎች።
  2. አይነት አንድ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች
  3. ከስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ ኪቶአሲዶሲስ (diabetic ketoacidosis) ያጋጠማቸው ሰዎች።

የግልፕዛይድ ትክክለኛ አወሳሰድ

የሀኪምዎን ትእዛዝ ይከተሉ።

ይህን መድሀኒት ምግብ ከመብላትዎ ከሰላሳ ደቂቃ በፊት ይዋጡ።

የታዘዘው የግልፕዛይን መድሀኒት አይነት ኤክስቴንድድ ሪሊዝ (extended-release) ከሆነ መስበር ማድቀቅ ወይም ማኘክ ጥሩ አይደለም።

መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?

ወድያው እንዳስታወሱ ይውሰዱ። ብዙ ሰአት ካለፈ ይተውት እና በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ጊዜ የተለመደውን መጠን ይዋጡ። የረሱትን ጨምረው ለመዋጥ አይሞክሩ። ለሀኪምዎ ሳያማክሩ ድንገት መድሃኒትዎን አያቁሙ።

የጎን ጉዳቶች (Side effects)

ይህን መድሀኒት የሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች ማቅለሽለሽ፣ ማስቀመጥ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት(drowsiness)፣ ራስምታት ሊሰማቸው ይችላል። ብዙ ግዜ መድሀኒቱን ሲጀምሩ አከባቢ የሚሰማ ህመም ነው። መድሀኒቱ ከሰውነት ጋር ሲላመድ ይተዋል። ካልተወ ወይም ከአቅም በላይ ከሆነ ግን ለሀኪምዎ ያሳውቁ።  

ይህን መድሀኒት ወስደው አልኮል መጠጣት ሀይለኛ የማቅለሽለሽ ስሜት ሊያመጣ ይችላል።

ይህን መድሀኒት ሲወስዱ የሰውነት ክብደት መጨመር ሊታይ ይችላል።

ስለሀይፖግላይስሚያ (Hypoglycemia) “ሌሎች ጥንቃቄዎች” በሚለው ርዕስ ስር ያንብቡ።

ይህ መድሀኒት የሀኪም ክትትል ያስፈልገዋል?

የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሀኪም ቤት ቀጠሮ መከታተል ያስፈልጋቸዋል። ይህ የሚደረገው

  1. የታዘዘላቸው መድሀኒት ስኳር በሽታቸውን ለመቆጣጠር እየረዳቸው መሆኑን ለማወቅ
  2. በመድሀኒቱ ምክንያት የሚመጡ የጎን ጉዳቶች እየተባባሱ እንዳልሆኑ ለማወቅ
  3. በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጡ ሌሎች ህመሞች (ለምሳሌ የኩላሊት በሽታ) ካሉ በጊዜ ለማወቅ እና የሚያስፈልገውን ህክምና ለማድረግ

በተጨማሪ የአይነቱ ሁለት የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከጊዜ በሁዋላ ጣፊያቸው ሙሉ በሙሉ ኢንሱሊን የማምረት ችሎታውን ሊያጣ ይችላል። በዚህ ጊዜ ይህ መድሀኒት አይሰራም። ይህን በምርመራ አረጋግጦ ሃኪማቸው ከግልፕዛይድ ወደሌላ መድሀኒት ሊለውጥላቸው ይችላል። ስለዚህ የህክምና ቀጠሮዎን መከታተል ጥሩ ነው።

ሌሎች ጥንቃቄዎች

መጀመሪያ የሚታዘዘው መድሀኒት መጠን የደም ግሉኮስን ወይም ኤዋንሲን (A1C) ላያስተካክል ይችላል። ስለዚህ ሀኪም ይህን መድሀኒት በትንሽ መጠን ጀምሮ ቀስ በቀስ እየጨመረ መሄድ ይፈልግ ይሆናል። የስኳር በሽታን መቆጣጠር እስከሚቻል ድረስ የመድሀኒቱ መጠን እያስተካከሉ መሄድ የመድሀኒቱን የጎን ጉዳት (side-effect) ለመቀነስ እና ለህመምተኛው የሚሆነውን ትክክለኛውን የመድሀኒት መጠን ለማግኘት ይጠቅማል።

ሀይፓግላይስሚያ (Hypoglycemia)፦ አንዳንድ ሰዎች ግልፕዛይድ ሲወስዱ የደም ግሉኮሳቸው መጠን ከሚፈለገው በታች ሊወርድ ይችላል።

የደም ግሉኮስ ሲለካ ከ70 በታች ሲሆን ወይም አንዳንድ የህመም ምልክቶች ሲታዩ የደም ግሉኮስ ከሚፈለገው በታች ነው (Hypoglycemia) ይባላል። እንደከፍተኛ የደም ግሉኮስ ሁሉ ይህ የደም ግሉኮስ በጣም ዝቅ ማለት ለጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል።

ይህን የጎን ጉዳት ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮች መድሀኒቱን ያለምግብ መውሰድ፣ በቂ ምግብ አለመመገብ፣ እና ሌሎች አንዳንድ መድሀኒቶች ናቸው።

ዋና ዋና የህመም ምልክቶቹ የረሀብ ስሜት፣ ያለተለመደ ግራ መጋባት (confusion)፣ ራስ ማዞር፣ የሰውነት መዛል፣ የመንቀጥቀጥ ስሜት፣  በላብ መጠመቅ፣ የልብ በሀይል መምታት፣ እንዲሁም ከባሰ እራስን መሳት ናቸው።

እነዚህ ምልክቶች የተሰማው ሰው ማድረግ ያለበት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው

  1. ከተቻለ የደም ግልሉኮስ መለካት
  2. ይህ ካልተቻለ ወይም ተለክቶ የደም ግልኮስ ከ70 በታች ከሆነ ስኳርነት ያለው ምግብ ወይም መጠጥ መውሰድ። ለምሳሌ የግሉኮስ ታብሌት፣ አንድ የሻይ ማንኪያ ስኳር፣ ከረሜላ፣ ግማሽ ብርጭቆ የብርቱካን ጭማቂ ወይም አንድ ብርጭቆ ወተት መውሰድ ይቻላል።
  3. ከ15 ደቂቃ በሁዋላ የደም ግሉኮስ ከ70 በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ደግሞ መለካት።
  4. ተለክተው ከ70 በላይ ከሆነ ቀለል ያለ ምግብ መመገብ
  5. ተለክተው አሁንም ከ70 በታች ከሆነ እንደገና ጣፋጭነት ያለው ምግብ መብላት እና ወደሀኪም ቤት መሄድ።
  6. ይህ አንዴ ካጋጠመ የስኳር በሽታዎን ለሚከታተል ሀኪምዎ መንገር አይርሱ።

የልብ ወይም የደም ስር በሽታ ላለበት ሰው ከግልፕዛይድ የተሻለ መድሀኒት ሊኖር ይችላል። መድሀኒት ለሚያዝልዎት ሀኪም ከዚህ በፊት የልብ ወይም የደም ስር በሽታ  አጋጥሞት ከነበረ መንገር አይዘንጉ።

የልብ ወይም የደም ስር በሽታ ላለበት ሰው ከግልፕዛይድ የተሻለ መድሀኒት ሊኖር ይችላል። መድሀኒት ለሚያዝልዎት ሀኪም ከዚህ በፊት የልብ ወይም የደም ስር በሽታ አጋጥሞት ከነበረ መንገር አይዘንጉ።

መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ

ይህ መድሀኒት የሚቀመጥበት ቦታ ሙቀት፣ ቅዝቃዜ እና እርጥበት የማይበዛበት ህጻናት የማይደርሱበት ቦታ ነው።

ማጣቀሻ

  1. American Diabetes Association. Pharmacologic Approaches to Glycemic Treatment: Standards of Medical Care in Diabetes-2020. Diabetes Care. 2020 Jan;43(Suppl 1):S98-S110. doi: 10.2337/dc20-S009.
  2. “Diabetes Mellitus.” Pharmacotherapy Handbook, by Barbara G. Wells et al., McGraw-Hill Education, 2017, pp. 161–175.
  3. Glucotrol – Glipizide Tablet , 2008, accessdata.fda.gov/drugsatfda_docs/label/2008/017783s019lbl.pdf.
  4. Management of Diabetes in Pregnancy: Standards of Medical Care in Diabetes—2021.” Diabetes Care, vol. 44, no. Supplement 1, 2020, doi:10.2337/dc21-s014.

ቀን: 01/15/21

ኩፓኖች