Amharic Health Information

የደም ግፊት ምርመራ

የደም ግፊት ምርመራ የሚደረገው ስፊግሞ-ማኖ-ሜትር( Sphygmomanometer) በሚባል የደም ግፊት መለኪያ መሳሪያ ነው። ወደሀኪም ቤት ሲሄዱ ይህ ምርመራ በአብዛኛው ይደረጋል። ከሀኪም ቤት ውጭ በየፋርማሲዎች  በሚገኙ የደም ግፊት መለኪያ መሳሪያዎች ራስዎን መመርመር እና የደም ግፊት ቁጥርዎን ማወቅ ይችላሉ። እንዲሁም ደግሞ  ይህን መሳርያ በግለሰብ ደረጃ ገዝቶ በቤት ውስጥ መጠቀም ይቻላል። በተለይ የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ይህ መሳርያ በቤታቸው ቢኖራቸው መልካም ነው። ከፍተኛ የደም ግፊትን በተገቢው ግዜ መርምሮ ማወቅና ህክምና ማድረግ በከፍተኛ ደም ግፊት የተነሳ የሚመጡ ተያያዥ በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከል ይረዳል።

ከፍተኛ የደም ግፊት ካለብዎት በቤት ውስጥ የደም ግፊትን በየግዜው መለካት አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ቤት ውስጥ የተለኩትን የደም ግፊት ውጤት መዝግበው ለሀኪምዎ ማሳየት ይመከራል። ይህም ሀኪምዎ የሚያዝልዎትን መድሃኒት ለመጨመር፣ ለመቀነስ ወይም ባለበት መቀጥል እንዳለበት ለመወሰን ይረዳል።

በሌላ መልኩ አንዳንድ ሰዎች ሆስፒታል ሄደው የሚለኩት የደም ግፊት ቁጥር ከተለመደው በላይ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል። ይህ የሚሆነው በተለያየ ምክንያት ሲሆን በዋነኝነት ግን በዋይት ኮት ሲንድሮም (White coat syndrome) ምክንያት ነው። ነጭ ኮት የለበሰ ሰው ስናይ የሚፈጠር መረበሽ የደም ግፊትን በተወሰነ ደረጃ ከፍ ሊያደርገው ይችላል። በመሆኑም በዚህ ቁጥር ብቻ ተነስቶ የሚታዘዝ መድሃኒት ከሚያስፈልገው በላይ ሊሆን ስለሚችል በቤትዎ የሚለኩት የደም ግፊት ቁጥርን ለሀኪምዎ  ማ ሳየት ጠቃሚ ነው።

የደም ግፊት መቼ እና በየስንት ግዜው መለካት አለበት

  • ሁሉም ጤነኛ የሆኑ አዋቂ ሰዎች ቢያንስ በአመት አንድ ግዜ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።
  • የደም ግፊት እንዳለብዎት በሃኪምዎ ከተነገረዎት በኋላ ቢቻል በየእለቱ የደም ግፊትዎን መለካት እና ውጤቱን መመዝገብ ጥሩ ነው። ይህ ካልሆነ ግን በሳምንት አንድ ቀን መለካት ይመከራል።
  • የደም ግፊትዎን የሚለኩበት ግዜ በተመሳሳይ ሰአት ቢሆን መልካም ነው። ጠዋት ከእንቅልፍዎ ከተነሱ በኋላ ወይም ማታ ወደመኝታዎ ከመሄድዎ ቀደም ብለው ቢያደርጉት መልካም ነው።

የደም ግፊት መለኪያ መሳሪያ አይነቶች

1. ማንዋል የደም ግፊት መለኪያ መሳርያዎች (Manual blood pressure monitors)

ማንዋል የደም ግፊት መለኪያ ክንድ ማሰሪያ፣ አየር ማስገቢያ ፊኛ እንዲሁም ማዳመጫ ስቴተስኮፕ(Stethoscopes) እና ውጤት ማንበቢያ ጌጅ ይኖረዋል። ይህ መሳሪያ በትክክል ከተጠቀሙበት የደም ግፊትዎትን መጠን በትክክል ይለካል። ማንዋል የደም ግፊት መለኪያ በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ የተመረጠ መሳሪያ ነው። ነገር ግን አጠቃቀሙ ላይ በቂ ስልጠና ካላገኙ በስተቀር ውጤቱን ማንበብ አደናጋሪ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በቤት ውስጥ ለመጠቀም ይህ ማንዋል የደም ግፊት መለኪያ አይመከርም።

manual blood pressure monitor
Photo by www.medisave.co.uk https://flic.kr/p/hfKw2m

2. ዲጂታል የደም ግፊት መለኪያ መሳሪያዎች (Digital blood pressure monitors)

ዲጂታል የደም ግፊት መለኪያ መሳሪያዎች ክንድ ላይ ወይም እጅ አንጓ በላይ(wrist cuff) የሚታሰር ማሰሪያ አላቸው። ከዚህ ጋር በቀጭን ቱቦ የተያያዘ የውጤት ማንበቢያ ዲጂታል ስክሪን(screen) ይኖራቸዋል።

ዲጂታል የደም ግፊት መለኪያ መሳሪያዎች ቤት ውስጥ ለመጠቀም ምቹ እና ቀላል ናቸው። ነገር ግን በሚጠቀሙበት ግዜ መንቀሳቀስ ወይም ማውራት የውጤቱን ጥራት ይቀንሰዋል።

የዲጅታል ደምግፊት መሳሪያዎች ሌላው ጥሩ ጎናቸው ውጤትዎትን መዝግበው ማስቀመጣቸው ነው። ስለዚህ ውጤትዎን መመዝገብ ከረሱ ፈልገው ማውጣት ይችላሉ። ወይንም መሳሪያዎትን እንዳለ ወደሀኪምዎ መውሰድ እና ውጤትዎን ከመሳሪያው ማስነበብ ይችላሉ።

photo by Dennis Sylvester Hurd at https://flic.kr/p/2hwvtjC

የደም ግፊት መለኪያ ማሰሪያ ርዝመት/ስፋት

ትክክለኛ ውጤት ለመለካት የደም ግፊት መለኪያ ማሰሪያ ርዝመት/ስፋት ወሳኝነት አለው። ማሰሪያው ሰፊ የሆነ እንደሆነ ከትክክለኛው የደም ግፊት በታች የሆነ ውጤት ይሰጣል። ከጠበበ ደግሞ የደም ግፊት ከትክክለኛው የደም ግፊት በላይ እንዲሆን ያደርገዋል። ስለዚህ የደም ግፊት መለኪያ መሳርያ በሚገዙበት ግዜ የማሰሪያው መጠን ለርስዎ የክንድ ውፍረት ተመጣጣኝ መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። በገበያ ላይ ያሉ የደም ግፊት መለኪያ መሳሪያዎች በአራት የተለያየ መጠን ይመጣሉ።

የማሰሪያ መጠንCuff sizeየክንድ ውፍረት ዙርያ በሴንቲሜትር
ትንሽ የአዋቂSmall adult22 – 26
የአዋቂAdult27 – 34
ትልቅ የአዋቂLarge adult35 – 44
በጣም ትልቅAdult thigh45 – 52

የደም ግፊትዎን ለመለካት የሚከተሉትን ቅደም ተከተሎች ይከተሉ

1. የደም ግፊትዎን ከመለካትዎ በፊት

  • ቡና ጠጥተው ሲጃራ አጭሰው ወይም ስፓርት ሰርተው ከነበረ ለ30 ደቂቃ እረፍት ያድርጉ። አለበለዚያ ቢያንስ ለ5 ደቂቃ ቁጭ ብለው እረፍት ያድርጉ።
  • የውሃ ሽንት ካለብዎ መጀመሪያ ሽንት ቤት ይጠቀሙ።
  • ሃሳብዎን እና ሰውነትዎን ለማረጋጋት ደስ የሚሉ ሃሳቦችን ለማሰብ ይሞክሩ።
  • ለመለካት ዝግጁ ሲሆኑ መደገፊያ ያለው ወንበር ላይ ይቀመጡ።
  • እጅዎትን የሚያስደግፉበት እና የመለኪያ መሳሪያውን የሚያስቀምጡበት ጠረጴቤዛ ያስፈልግዎታል።
  • ጀርባዎን ቀጥ አድርገው የወንበሩ መደገፊያ ላይ ደገፍ ለማለት ይሞክሩ።
  • ሁለቱም እግርዎችዎ መሬት ላይ ያሳርፉ። እግርዎ መጣመር (መነባበር) የለበትም።

2. የደም ግፊትዎን በሚለኩበት ግዜ

  • የሚለኩበት ክንድ ላይ የለበሱትን ልብስ ያውልቁ። ልብስዎን ወደላይ አይሰብስቡ። እንዲህ ማድረግ የደም ግፊትዎን መጠን ሊጨምር ይችላል።
  • የደም ግፊት መለኪያ ማሰሪያ ሲያስሩ ከክንድዎ መታጠፊያ ትንሽ ከፍ ማለቱን ያረጋግጡ። ማሰሪያው በሃይል መጥበቅ ወይም በጣም መላላት የለበትም።
Arm bp proper posture
ክንድ ላይ የሚታሰር የደም ግፊት መለኪያ
  • የእጅ አንጓ ላይ የሚታሰር መለኪያ ከሆነ ክርንዎን ጠረቤጴዛ ላይ አስደግፈው የእጅዎን እንጓ ከልብዎ ትይዩ እስከሚሆን ከፍ ያድርጉት።
wrist bp cuff
እጅ ላይ የሚታሰር የደም ግፊት መለኪያ
  • የክንድ ማሰሪያውን እና የመለኪያ መሳሪያውን የሚያገናኘው ቀጭን ቱቦ ክንድዎ መካከል እንዲሆን ያስተካክሉት። ይህ ቱቦ መጠላለፍ የለበትም። እንዲሁም ምንም ነገር እንዳልተጫነው ያረጋግጡ።
  • መለካት ለመጀመር “START” ወይም “ON” የሚለውን ቁልፍ ከተጫኑ በኋላ ማውራት ወይም እንቅስቃሴ ማድረግ አያስፈልግም።

3. የደም ግፊትዎን ከተለኩ በኋላ

  • ውጤቱን እንዲሁም የተለኩበትን ቀንና ሰአት ይመዝግቡ።
  • ከተለመደው ከፍ ወይም ዝቅ ያለ ከሆነ ቢያንስ አንድ ደቂቃ ቆይተው እንደገና የደም ግፊትዎን ይለኩ። ሁለተኛውን የደም ግፊት ቁጥር ይመዝግቡ።
  • የመዘገቡትን የደም ግፊት ቁጥሮች ለሀኪምዎ ማሳየት አይርሱ።

የደም ግፊት ቁጥሮች

የደም ግፊት ሲለኩ ሁለት ቁጥሮችን ያያሉ። በተለምዶ እነዚህ ቁጥሮች የላይኛው (ሲስቶሊክ/systolic blood pressure) እና  የታችኛው (ዳያስቶሊክ/diastolic blood pressure) ይባላሉ።

  • የላይኛው(ሲስቶሊክ/systolic) ቁጥር የሚያመላክተው ልብ ሲመታ በደም ስር ላይ የሚያሳርፈውን የግፊት መጠን ነው።
  • የታችኛው(ዳያስቶሊክ/diastolic) ቁጥር የሚያመላክተው ልብ ሲያርፍ ወይም በሁለት የልብ ምቶች መካከል በደም ስር ላይ ያለው የደም ግፊት ነው።

የከፍተኛ ደም ግፊት ምርመራ ሁለቱንም የደም ግፊት ቁጥሮች ግምት ውስጥ ያስገባል። ከሁለቱ አንዱ ወይም ሁለቱም ከፍተኛ ከሆነ ሃኪምዎ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳለብዎ ሊነግርዎ እና መድሃኒት ሊያዝልዎ ይችላል።

የአሜሪካን ልብ አሶስየሽን (AHA/ACC) የከፍተኛ ደም ግፊት መደቦች

የላይኛው(systolic blood pressure)

የታችኛው (diastolic blood pressure)

ጤናማ ከ120 mmHg በታች ከ80 mmHg በታች
ከፍ ያለ የደም ግፊት 120 – 129 mmHg 80 mmHg
ደረጃ አንድ ከፍተኛ የደም ግፊት 130 – 139 mmHg 80-89 mmHg
ደረጃ ሁለት ከፍተኛ የደም ግፊት ከ140 mmHg በላይ ከ90 mmHg በላይ
አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልገው የደም ግፊት ከ180 mmHg በላይ ከ120 mmHg በላይ
ጤናማ የደም ግፊት (Healthy blood pressure)

ዘወትር ሲለካ የደም ግፊት ቁጥር ከ 120/80 በታች ከሆነ ጤናማ ነው። በዚሁ ለመቀጠል ጤናማ አመጋገብ እንዲሁም የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ከፍ ያለ የደም ግፊት (Elevated blood pressure)

በተለያየ ግዜ የደም ግፊት ሲለካ ከ 120/80 አስከ 129/89 ከሆነ ለፍተኛ የደም ግፊት መጋለጥን ያመላክታል። የደም ግፊት እየጨመረ እንዳይመጣ በምግብ ውስጥ የሚጨምሩትን ጨው መጠን መቀነስ፣ የአካል እንቅስቃሴ መጨመር፣ ውፍረትን መቀነስ እንዲሁም ሌሎች የደም ግፊት ለማስተካከል የሚረዱ የኑሮ ዘይቤዎችን መከተል ይመከራል።

ደረጃ አንድ ከፍተኛ የደም ግፊት (High blood pressure stage 1)

የደም ግፊት ቁጥር በተደጋጋሚ ከ 130/80 እስከ 139/89 ከሆነ ሀኪም ቤት መሄድ ያስፈልጋል። ዶክተርዎ የደም ግፊትዎን በተለያየ ቀን በመለካት እንደአስፈላጊነቱ መድሃኒት ሊያዝልዎ ይችላል። የደም ግፊት ቁጥር በጨመረ ቁጥር በደም ግፊት ምክንያት የሚመጡ ሌሎች የልብ እና ደምስር ህመሞችን የማስከተል እድሉ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ መድሃኒትዎን ሀኪም እንዳዘዘልዎ መውሰድ ብቻ ሳይሆን በአመጋገብ እና በአካል እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ለውጥ ማሳየት ያስፈልጋል። መድሃኒትዎን ለሀኪምዎ ሳያማክሩ አያቋርጡ። የሀኪም ቤት ቀጠሮ ይከታተሉ።

ደረጃ ሁለት ከፍተኛ የደም ግፊት (High blood pressure stage 2)

የደም ግፊት ቁጥር በተደጋጋሚ ከ 140/90 በላይ ከሆነ የደም ግፊትዎን ለማስተካከል ሀኪምዎ ከአንድ በላይ መድሀኒት ሊያዝልዎት ይችላል። ልክ እንደ ደረጃ አንድ ከፍተኛ ደም ግፊት ሁሉ የደም ግፊትዎን ለማስተካከል መድሃኒት ሀኪምዎ እንደመከረዎ መውሰድ እና የአካል እንቅስቃሴ እንዲሁም አመጋገብ ላይ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል።

አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልገው የደም ግፊት (Hypertensive crisis)

የደም ግፊትዎን በቤትዎ ሲለኩ ከ180/120 በላይ ከሆነ አምስት ደቂቃ ቆይተው እንደገና ይለኩ። ውጤቱ ተመሳሳይ ከሆነ ለሀኪምዎ ደውለው መንገር ወይም ወደሀኪም ቤት መሄድ ያስፈልጋል። የደም ግፊትዎ ከ180/120 በላይ ሆኖ ሀይለኛ የራስ ምታት፣ ደረት ላይ የህመም ስሜት፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የአይን ብዥታ፣ ወይም የሰውነት መደንዘዝ ምልክቶች ካሉ ቶሎ ሀኪም ቤት መሄድ ያስፈልጋል

ማጣቀሻ

  1. “2017 ACC/AHA/AAPA/ABC/ACPM/AGS/APhA/ASH/ASPC/NMA/PCNA Guideline for the Prevention, Detection, Evaluation, and Management of High Blood Pressure in Adults.” Guideline . 2018.
  2. Blood pressure monitors for home: MedlinePlus Medical Encyclopedia. (n.d.). Retrieved July 21, 2020, from https://medlineplus.gov/ency/article/007482.htm
  3. Beevers, G., Lip, G. Y., & O’Brien, E. (2001, April 14). Mendability. Retrieved August 01, 2020, from https://www.facebook.com/Mendability/posts/3060605373987732
  4. Commissioner, O. (n.d.). High Blood Pressure – Medicines to Help You. Retrieved July 25, 2020, from https://www.fda.gov/consumers/free-publications-women/high-blood-pressure-medicines-help-you
  5. Potassium Fact Sheet for Health Professionals. 3 June 2020. website. 23 July 2020. <https://ods.od.nih.gov/factsheets/Calcium-HealthProfessional/#h7>.
  6. Understanding Blood Pressure Readings. (n.d.). Retrieved July 21, 2020, from https://www.heart.org/en/health-topics/high-blood-pressure/understanding-blood-pressure-readings

 

ቀን: Aug, 07, 2020