የስኳር በሽታ - ዳያቤቲስ - Diabetes
የስኳር በሽታ በደም ውስጥ ከመጠን በላይ ግሉኮስ ሲኖር የሚፈጠር በሽታ ነው። የዚህ መንስኤ በተፈጥሮ ከጣፊያ የሚመነጭ ኢንሱሊን የተባለ ኬሚካል በቂ በሆነ መጠን ወይ ፈጽሞ አለመመረት ነው።
ግሉኮስ ስኳርነት ካላቸው ምግቦች የሚገኝ ለሰውነት ጉልበት የሚሰጥ ንጥረ ነገር ነው። ኢንሱሊን በደም ውስጥ ያለ ግሉኮስ ወደሚፈለግበት የሰውነት ክፍል እንዲገባ ያደርጋል። ለምሳሌ ጡንቻ እና ሌላ የሰውነት ክፍሎች ቤቶች ከሆኑ፤ ግሉኮስ ወደቤቱ እንዲገባ የሚያደርገው ቁልፍ ኢንሱሊን ነው። ኢንሱሊን ከሌለ፤ በደም ውስጥ ያለው ግሉኮስ ወደሚፈለግበት የሰውነት ክፍል አይገባም። ከምግብ የሚገኘው ግሉኮስ በደም ውስጥ እየገባ መከማቸቱ ይቀጥላል። ስለዚህ የደም የግሉኮስ መጠን እየጨመረ ይሄዳል። ይህም የስኳር በሽታ ዋና ምልክት ነው።
ሶስት አይነት የስኳር በሽታ አይነቶች አሉ።
- አይነት አንድ (Type I diabetes)፦ ብዙ ግዜ በልጅነት ይጀምራል። በሽተኞች በሰውነታቸው ውስጥ ኢንሱሊን አይመረትም። ስለዚህ ምትክ ኢንሱሊን ያስፈልጋቸዋል።
- አይነት ሁለት (Type II diabetes)፦ ብዙ ግዜ በጎልማሶች እና በአዛውንቶች ላይ ይታያል። በመጀመሪያ የኢንሱሊን ማምረቻ (ጣፊያ) ስራውን ይቀንሳል። ቀስ በቀስ ግን የኢንሱሊን ምርት ይቆማል። ለህመምተኞች የህክምና ክትትል ያስፈልጋቸዋል። የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እና የአመጋገብ ልማድን መለወጥ የህክምናው አካል ነው
- በእርግዝና ግዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ (Gestational diabetes)፦ ይህ በእርግዝና ግዜ የደም ግሉኮስ መጨመር በሚገባ ህክምና ካልተደረገለት የእናት እና የጽንሱ ጤንነት ላይ አደጋ ይጥላል። ብዙ ሴቶች ከወለዱ በሃላ የደም ስኳር መጠን ይስተካከላል።
የስኳር በሽታ ዋና ምልክቶች
የማይቆርጥ የውሃ ጥም፣ የረሃብ ስሜት፣ ቶሎ ቶሎ የውሃ ሽንት ማስቸገር ናቸው።
በተጨማሪ የቆዳ መድረቅ፣ ድካም፣ ቁስል ለመዳን ረጅም ግዜ መፍጀት፣ እና አይን ብዥታ ሌሎች የስኳር በሽታ ምልክቶች ናቸው።
የስኳር በሽታን ለመርመር የሚረዱ ሁለት መንገዶች አሉ።
- የመጀመሪያው ከጣት ላይ ጠብታ ደም በመውሰድ ደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መለካት ነው። ጤናማ ሰው በባዶ ሆድ የደም ስኳሩ ሲለካ ከ126 በታች ይሆናል። ከምግብ በሃላ ከተለካ ከ180 በታች ይሆናል።
- የኤዋንሲ (A1C) ምርመራ በደም ላይ የሚደረግ ሲሆን፣ ላለፉት ሶስት ወራት በደም ውስጥ ያለውን አማካኝ የግሉኮስ መጠን ይገልጻል። ጤናማ ሰው የኤዋንሲው ውጤት ከ6.5% በታች ነው።
የስኳር በሽታ ማዳን ወይም እንዳይከሰት ማድረግ አይቻልም። ነገር ግን ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ህመሞችን መቀነስ እና ማዘግየት የስኳር በሽታ ህክምና ዋና አላማ ነው። የደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በህክምና፤ በምግብ፤ እና በሰውነት እንቅስቃሴ በመቀነስ፤ ረጅም እና ጤናማ እድሜ መኖር ይቻለል።
ማጣቀሻ
በቅርብ ግዜ የወጡ ጽሁፎች
- ቅድመ ስኳር በሽታ (Pre-diabetes)
በደም ውስጥ ያለ ግሉኮስ መጠን ሲጨምር ነገር ግን የስኳር በሽታን ያህል ከፍተኛ ካልሆነ ቅድመ ስኳር…
- ሜትፎርሚን (Metformin HCL)
ሜትፎርሚን፤ ስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች፤ በደማቸው ያለውን የግሉኮስ መጠን በአግባቡ ለመቀነስ የሚታዘዝ መድሃኒት ነው።
14 thoughts on “ስኳር በሽታ”
Comments are closed.